የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ሴኔጋል በፊፋ የዓለም ሀገራት ወርሃዊ ደረጃ ወደ 12ኛ ደረጃ ከፍ አለች - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ሴኔጋል በፊፋ የዓለም ሀገራት ወርሃዊ ደረጃ ወደ 12ኛ ደረጃ ከፍ አለች
አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2018(ኢዜአ):- የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) ወርሃዊ የሀገራት የእግር ኳስ ደረጃን ይፋ አድርጓል።
በዚህም የ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ባለድሏ ሴኔጋል ሰባት ደረጃዎችን በማሻሻል ከነበረችበት 19ኛ ደረጃ ወደ 12ኛ ከፍ ብላለች።
በፍጻሜው ሽንፈት ያስተናገደችው ሞሮኮ ደግሞ ከ11ኛ ወደ 8ኛ ከፍ ብላለች።
በውድድሩ ሶስተኛ ደረጃ ይዛ ያጠናቀቀችው ናይጄሪያ 12 ደረጃዎችን በማሻሻል 26ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
አልጄሪያ 28ኛ፣ ግብጽ 31ኛ፣ ኮትዲቯር 37ኛ፣ ካሜሮን 45ኛ፣ ቱኒዚያ 47ኛ፣ ማሊ 54ኛ፣ ደቡብ አፍሪካ 60ኛ እና ቡርኪና ፋሶ 62ኛ ደረጃን ይዘዋል።
ኢትዮጵያ በታህሳስ ወር በነበረችበት 147ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ስፔን፣ አርጀንቲና፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ እና ብራዚል ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
ፖርቹጋል እና ኔዘርላንድስ ስድስተኛ እና ሰባተኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ ሳን ማሪኖ የመጨረሻውን 210ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
የቡድን ጥንካሬ፣ የሚደረገው ጨዋታ ያለው ወሳኝነት፣ የጨዋታ ውጤትና ከጨዋታ በፊት የሚጠበቅ ውጤት ፊፋ የሀገራትን የእግር ኳስ ደረጃ የሚለከባቸው መመዘኛዎች ናቸው።