ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶቹ ሀገሪቱን የብልፅግና ተምሳሌት የሚያደርጉ በመሆናቸው ለውጤታማነታቸው ህዝቡ በጋራ መቆም ይኖርበታል - ኢዜአ አማርኛ
ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶቹ ሀገሪቱን የብልፅግና ተምሳሌት የሚያደርጉ በመሆናቸው ለውጤታማነታቸው ህዝቡ በጋራ መቆም ይኖርበታል
ጭሮ፤ ጥር 12/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት የጀመራቸው ግዙፍ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን በአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት የሚያደርጉ በመሆናቸው ለውጤታማነታቸው ህዝቡ በጋራ መቆም አለበት ሲሉ የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለፁ።
ምሁራኑ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት መንግስት የጀመራቸው የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የተፈጥሮ ጋዝ ማጣሪያ፣ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እና ሌሎች ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን በአፍሪካ ደረጃ የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ከፍተኛ አቅም አላቸው።
በዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ሀላፊ ጂፋራ ለሜሳ እንዳሉት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶቹ ሀገሪቱ ገቢ ምርቶችን በራሷ አቅም በማምረት የውጭ ምንዛሬን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ የሚያስችሉ ናቸው።
መንግስት እንደነዳጅ እና ማዳበሪያ ያሉ ገቢ ምርቶችን ለመግዛት የሚያውጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ
ለማዳንና ተኪ ምርቶችን በማምረት ልማትን ለማፋጠን እንደሚያስችሉም ጠቅሰዋል።
በተለይም የአፈር ማዳበሪያ ፕሮጀክቱ አርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ እና በበቂ መጠን ማዳበሪያ እንዲያገኝ እና የግብርና ምርቶች መጠን እንዲጨምር እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የማዳበሪያ ፋብሪካው እንደ ሕዳሴው ግድብ ኢትዮጵያ ከራሷ ባለፈ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝና ከሌሎች ጋር አብሮ ለማደግ ትልቅ እገዛ የሚያደርግላት መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም እነዚህ ትልቅ ተስፋን የሰጡ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲሳኩ ሁሉም በጋራ በመቆም መረባረብ አለበት ብለዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ወቅት የተበሰሩ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጡና የሀገሪቱን ብልፅግና ዕውን የሚያደርጉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የትምህርት ክፍሉ መምህር ኢስማኤል ሁሴን ናቸው።
የልማት ፕሮጀክቶቹ በሚቀጥሉት አምስትና ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያን የአፍሪካ የለውጥና የብልፅግና ተምሳሌት እንድትሆን አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይ ለሰላማዊ አገልግሎት የሚውል የኒውክሌር ተቋም ለመገንባት የተጀመረው ስራ በጤና ተቋማት ዘመናዊ አገልግሎትና በሌሎች ዘርፎች ከሚኖረው ጠቀሜታ በተጨማሪ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን አቅም የሚያሳድግና የምርምር ዘርፉን የሚያዘምን መሆኑን አብራርተዋል።
እነዚህ ውጥኖች ወደ መሬት እንዲወርዱ ምሁራንን ጨምሮ በየደረጃው ያለ የህብረተሰብ ክፍል ሚናውን መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል ሀላፊ ነዋይ ጎርባቾ በበኩላቸው በቀጣይ የሚገነቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ብልፅግናን ከማረጋገጥ ባለፈ በዲፕሎማሲው መስክ ተፅዕኖ ፈጣሪና ጠንካራ ሀገር እንድትሆን የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።
የቢሾፍቱ ዓለምአቀፍ አየር ማረፊያ የኢትዮጵያን አቪዬሽን አቅም የሚያሳድግና ኢትዮጵያም በዘርፉ ከዓለም ታላላቅ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት መንግስት ለፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት መጠናቀቅ የሰጠው ትኩረት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶቹን በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት በከፍተኛ ቁርጠኝነት የሀሪቱን ብልፅግና ለማረጋገጥ ለጀመረው ጥረት ምሁራን፣ ባለሀብቶችና መላው ህዝብ በቁጭትና በንቃት ድጋፉን ሊሰጥ እንደሚገባም ጨምረው አስታውቀዋል።