የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2018(ኢዜአ)፦ የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 'CBE Connect Digital Wallet' የተሰኘ ከውጭ ሀገር ገንዘብ ለመላክ የሚያስችል አዲስ መተግበሪያ ስራ አስጀምሯል።
አዲሱ መተግበሪያ የበለጸገው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ስታር ፔይ ፋይናንሻል ሶሉሽንስ ትብብር መሆኑ በመርሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል።
በአገልግሎት ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በወቅቱ የባንኩ ፕሬዝዳንት ተወካይና የኮርፖሬት አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ኤፍሬም መኩሪያ እንደገለጹት ባንኩ አሰራሩን በየወቅቱ በማዘመን ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ባንኩ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት ደንበኞች ቀልጣፋ ተደራሽ እና ዘመናዊ አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።
ዛሬ ስራ የጀመረው መተግበሪያ የባንኩን የዲጂታል ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑንም ገልጸዋል።
ዲጂታል አገልግሎቱ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ ደንበኞችን ይበልጥ የሚያስተሳስርና የሐዋላ ሂደትን የሚያቀላጥፍ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ ዲጂታል ቴክኖሎጂው የተለያዩ የመገበያያ ገንዘቦችን ማስተናገድ መቻሉ ተጠቃሚዎች እንደ ፍላጎታቸው እንዲገበያዩ ዕድል የሚሰጥ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ተደራሽነቱን ለማስፋት የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀዋል።
የስታር ፔይ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሱፍቃድ ጌታቸው በበኩላቸው፤ ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዲጂታል ሥርዓት ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት ለቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የፈጠረው ምቹ ሁኔታ መሰል ፈጠራዎች እንዲበራከቱ ማድረጉን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማበልጸግ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።