ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምን በማረጋገጥ ረገድ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እያስመዘገበች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምን በማረጋገጥ ረገድ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እያስመዘገበች ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የወል ትርክትን በመገንባትና ብሔራዊ ጥቅምን በማስጠበቅ ረገድ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እያስመዘገበች መሆኗን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ያሏት ፀጋዎች ሁለንተናዊ ዕድገትን ለማምጣት እና ዜጎችን የሚያስተሳስር የጋራ ትርክት ለመገንባት ወሳኝ ናቸው።
እነዚህን ፀጋዎች በውል ተገንዝቦ ሀገራዊ ፋይዳ ላለው ተግባር ማዋል ባለመቻሉ እና በሚያስተሳስሩን ጉዳዮች ላይ ትኩረት ባለመደረጉ ሀገራዊ ዕድገት ተገድቦ ቆይቷል ብለዋል።
በአንፃሩ አሁን ላይ ተገቢውን ትኩረት ያገኘው የጋራ ትርክት ጉዳይ እነዚህን ማነቆዎች በመፍታት ለሀገር ብልጽግና መሠረት እንደሚሆን አመላክተዋል።
የለውጡ መንግሥት አብሮነትን የሚያጎሉ የጋራ ትርክት ግንባታ ላይ እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተጽፈው ለንባብ የበቁት የመደመር መጻሕፍት፤ ዜጎች ስለ ሀገራቸው ያላቸውን አረዳድ በማስተካከልና የወል ትርክትን በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል።
በሀገሪቱ በተግባር ዕየታዩ የሚገኙ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች የዜጎችን አንድነት ከማጠናከር ባለፈ ውስጣዊ ጥንካሬንና ብሔራዊ ኩራትን ማጎልበት የሚችል ዐቅም መፈጠሩንም ተናግረዋል፡፡
ይህም ለትውልድ ቀረጻና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ የሚውል የጋራ ትርክት የመፍጠር ሥራ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ያመላክታል ነው ያሉት።
ፈጠራ የታከለበት የመንግሥት ፈጣን አስተሳሳሪ የልማት አካሄድ፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንድታስከብር ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው በአጽንኦት አንስተዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከናወኑ የብሔራዊ ትርክት ግንባታ ሥራዎች ኢትዮጵያ ውስጣዊ አንድነቷን እንድታጠናክርና ጥቅሞቿን እንድታስከብር ዕድል መፍጠራቸውንም ጠቁመዋል።
ይህም ሀገሪቱ ሉዓላዊነቷንና ጥቅሟን በማረጋገጥ ረገድ ወሳኝ ሀገራዊ የከፍታ ምዕራፍ ላይ መድረሷን የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና የባሕር በር ባለቤትነትን የማረጋገጥ ጥረቶችን በዋነኛ ማሳያነት ጠቅሰዋል።
እነዚህም ኢትዮጵያ ያላትን ትልቅ ዐቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስመሰከሩና ዜጎችን በአንድ የጋራ ዓላማ ሥር ያሰለፉ መሆናቸው ነው የገለጹት።
በሕዳሴ ግድብ አማካኝነት ከራሷ አልፋ ለጎረቤት ሀገራት በቀጣናዊ የኃይል ትስስር ረገድ ያበረከተችውን ሚና ዓለም እንዲያውቀው አስችሏልም ብለዋል።
ፍትሐዊ የባሕር በር ባለቤትነትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ታሪካዊ ግስጋሴም፣ የጋራ ትርክት መገንባት ዜጎችን በአንድ ልብ ለማሰለፍ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።