ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በመፍታት ሀገርን በጋራ የመገንባት ሂደትን ያሳልጣል

አምቦ፤ ጥር 12/2018 (ኢዜአ)፡- ችግሮችን በምክክር በመፍታት ሀገርን በጋራ የመገንባት ሂደት እውን እንዲሆን የጎላ ሚና ላለው ሀገራዊ ምክክር ስኬት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን አባገዳዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መሠረታዊ የሆኑ ሀገራዊ የሐሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶችን ለመፍታት አካታች ምክክሮችን በማካሄድ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እየሠራ ይገኛል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአምቦ ከተማ አባገዳዎች እና የሀገር ሽማግሌዎችም፤ ምክክሩ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ወካይ ሐሳባቸውን የሚያቀርቡበት ትልቅ ሂደት መሆኑን ተናግረዋል።


 

አባገዳ ለገሠ ዳባ ምክክር የሚደገፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ በገዳ ሥርዓትም ምክክር ትልቅ ስፍራ እንደሚሰጠው አስገንዝበዋል።

እየተካሄደ ባለው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል እየተሳተፈ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ ብለዋል።

የከተማውን ሕብረተሰብ በመወከል በአዲስ አበባና አዳማ ከተሞች በምክክር ሂደቱ መሳተፋቸውን ገልጸው፤ በመድረኮቹ ለሀገር አንድነት የሚጠቅሙ ሐሳቦች መስጠታቸውን ገልጸዋል።

በምክክሩ ዙሪያ ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ ሲፈጥሩ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ ምክክሩ የታለመውን ውጤት እንዲያመጣ የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።


 

አባ ገዳ ታሪኩ ቱራ በበኩላቸው፤ የሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የቆዩ ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ የወደፊቷን ኢትዮጵያ የተሻለች ለማድረግ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን በአጽንኦት አንስተዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ዋናው ምክክርም በተሳካ መልኩ እንዲካሄድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ገንቢ ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።

የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያመጣ ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ በማስጨበጥም ሆነ በሌሎች መንገዶች የድርሻቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል።


 

ምክክር መቀራረብን በማጠናከር የተሻለች ሀገር ለመገንባት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ያስገነዘቡት ደግሞ የሀገር ሽማግሌ በቀለ ባየታ ናቸው።

ሀገራዊ ምክክሩ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን እንዲሁም የተጀመሩ ሀገራዊ ፕሮጀከቶች እንዲሳኩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ ለምክክሩ ስኬታማነት ድጋፋችን ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም