ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ለዲጂታል ዲፕሎማሲ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የዘመኑን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በመጠቀም የሀገርን ገጽታ ለማስተዋወቅ እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ለዲጂታል ዲፕሎማሲ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ። 

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲጂታል ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ስላባት ማናዬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ዲጂታል ዲፕሎማሲ የአንድን ሀገር ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በስትራቴጂያዊ መንገድ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኝ ወሳኝ መሣሪያ ነው ብለዋል። 

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተተገበረው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ለዲጂታል ዲፕሎማሲ ስራ ምቹ ምህዳር መፍጠሩንም አስታውሰዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ትኩረት የሚያደርግ በመሆኑ ለዘርፉ ትልቅ ዕድል ይዞ እንደሚመጣ ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ የልህቀት ማዕከል ለመሆን የምታደርገው ጉዞ ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ የሚደግፍ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቀጣይ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንሲ አማካኝነት ተገልጋዮች ወደ ቆንስላዎች በአካል መሄድ ሳያስፈልጋቸው በስልካቸው አገልግሎት የሚያገኙበት አሰራር እንደሚዘረጋም ጠቁመዋል። 

በህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጉብኝት ወቅት ይፋ የተደረገው የዳታ ማዕከል ግንባታም ዲጂታል ዲፕሎማሲውን ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ያላትን ተመራጭነት አንስተውም፤ ሀገሪቱ ለመካከለኛው ምስራቅ፣ ለእስያና ለአውሮፓ ያላት አማካይ መገኛ እና ለቀይ ባህር ያላት ቅርበት ሁነኛ የዲፕሎማሲ አጋር ያደርጋታል ብለዋል። 

የቱሪዝም ዲፕሎማሲ ስራም በዲጂታል ዲፕሎማሲ በኩል እየተከናወነ እንደሚገኝ ጨምረው ገልፀዋል።

ለዚህም ተፈጥሯዊና ስትራቴጂያዊ ጸጋዎች እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተገነቡት የቱሪዝም መዳረሻዎችን በዲጂታል አማራጮች ለዓለም የማስተዋወቅ ስራን በአብነት ጠቅሰዋል። 

21ኛው ክፍለ ዘመን የትርክት የበላይነትን ለመቆጣጠር የሚደረግ የመረጃ ውድድር ያየለበት ወቅት መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።

በሚቀያየረው የቴክኖሎጂ አውድ ውስጥ ተዋናይ ለመሆን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃን በዲጂታል ዲፕሎማሲው በመተንተንና ቀድሞ በመተንበይ ለሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም መከበር ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም