በሻምፒዮንስ ሊጉ ኢንተር ሚላን ከአርሰናል የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሻምፒዮንስ ሊጉ ኢንተር ሚላን ከአርሰናል የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2018 (ኢዜአ)፦ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሰባተኛ ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ይካሄዳሉ።
ምሽት 5 ሰዓት ላይ በሳን ሲሮ ስታዲየም ኢንተር ሚላን ከአርሰናል የሚያደርጉት ጨዋታ የተመልካቾችን ቀልብ ስቧል።
ኢንተር ሚላን እስከ አሁን ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች 12 ነጥብ በማግኘት 6ኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው አርሰናል በ18 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በዘንድሮው ሻምፒዮንስ ሊግ ሁሉንም ጨዋታዎች ያሸነፈ ብቸኛው ክለብ ነው።
ሁለቱ ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሲገናኙ የአሁኑ ለ4ኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 3 ጨዋታዎች አርሰናል ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪው አንድ ጨዋታ ኢንተር ሚላን ድል ቀንቶታል።
ቡድኖቹ ለመጨረሻ ጊዜ በአውሮፓ መድረክ የተገናኙት እ.አ.አ በ2024/25 ነበር። በወቅቱ ኢንተር ሚላን ሃካን ቻላንኦግሉ በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠረው ግብ 1 ለ 0 አሸንፏል።
ኢንተር ሚላን የሴሪ አ እና አርሰናል የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መሪ ናቸው።
የጣልያኑ ክለብ 3 ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አንስቷል። የሰሜን ለንደኑ አርሰናል ሻምፒዮንስ ሊግን አሸንፎ አያውቅም።
ሁለቱ ክለቦች በጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሌሎች መርሐ-ግብሮች ስፖርቲንግ ሊዝበን ከወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ፒኤስጂ፣ ሪያል ማድሪድ ከሞናኮ፣ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ፣ ኮፐንሃገን ከናፖሊ፣ ቪያሪያል ከአያክስ እና ኦሎምፒያኮስ ከባየር ሌቨርኩሰን በተመሳሳይ ከምሽቱ አምስት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ ቦዶ ግሊምት ከማንችስተር ሲቲ እና ካይራት አልማቲ ከክለብ ብሩዥ ይጫወታሉ።