ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ ጥር 12 /2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ መቀሌ 70 እንደርታ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ  በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

መቀሌ 70 እንደርታ በሊጉ እስከ አሁን ያሸነፈው ጨዋታ ብዛት ሁለት ብቻ ነው። ስድስት ጊዜ ሲሸነፍ ሰባት ጊዜ አቻ ተለያይቷል። በ15ቱ ጨዋታዎች ላይ 10 ግቦችን ሲያስቆጥር 19 ጎሎች ተቆጥረውበታል። 

ቡድኑ በ13 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

በሊጉ ካከናወናቸው 15 ጨዋታዎች መካከል ስድስቱን ያሸነፈው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ ሁለት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሰባት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 10 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ስድስት ጎሎችን አስተናግዷል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ25 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። 

ጨዋታው መቀሌ 70 እንደርታ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ነው። 

ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ወላይታ ድቻ ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

ወላይታ ድቻ በ13 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ባህር ዳር ከተማ በ20 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል። 

ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች አላሸነፈም። ባህር ዳር ከተማ በ15ኛ ሳምንት ከመቀሌ 70 እንደርታ ጋር ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል። 

ሁለቱም ቡድኖች ወደ ማሸነፍ መንገድ ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ፋሲል ከነማ ከሀዲያ ሆሳዕና ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በበዓሉ ምክንያት እንደማይካሄድ እና በቀጣይ በሚገለጽ ጊዜ በተስተካካይ መርሃ ግብር እንደሚደረግ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።

የ16ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ጥር 14 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

ሲዳማ ቡና ሊጉን በ30 ነጥብ እየመራ ነው። 

የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ አቤል ያለው በስምንት ግቦች እየመራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም