ቀጥታ፡

የጥምቀት በዓል የበጎነት፣የፍቅርና የአንድነት ማሳያ ነው 

አዲስ አበባ፤ጥር 11/2018 (ኢዜአ)፦የጥምቀት በዓል የትህትና፣ የበጎነት፣የፍቅርና የአንድነት ማሳያ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶች ገለፁ።   

የጥምቀት በዓል በደማቅ ሁኔታ በአዲስ አበባ ጀንሜዳ ተከብሯል፤ አከባበሩ ላይ  የሀይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣በርካታ ምዕመናን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ተገኝተዋል።

በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በዓል አከባበር ላይ የታደሙና ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የሃይማኖት አባቶች እንዳሉት የጥምቀትን በዓል ስናከብር ርህራሄ፣ ፍቅርና አንድነትን በመጠበቅ ሊሆን ይገባል።

በቀጨኔ ደብረሰላም መድሃኒአለም አገልጋይ የሆኑት መልአከብርሃን በልደ ወርቁ፤ ክርስቶስ በጥምቀቱ ያሳየውን ትህትና ሁላችንም ዝቅ ብለን እንድናገለግልና እንድንተባበር የሚያደርገን በመሆኑ ይህን አስተምህሮ በመተግበር ለአንድነትና ለሰላም መትጋት ይኖርብናል ሲሉ ገልጸዋል።


 

ከኢትዮጵያ በዩኔስኮ ከተመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ የሆነው የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ የሚከበር አስደናቂ ትዕይንት የሚታይበት በዓል መሆኑንም አመልክተዋል።

መጋቢ ሃዲስ ለማ በየነ በበኩላቸው የጥምቀት በዓል የሕዝቦች አንድነት፣ ፍቅር፣ ትህትና እና አብሮነት የሚንፀባረቅበት ልዩ በዓል እንደሆነም ተናግረዋል።


 

በዚህም የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ ያለው ለሌለው በመረዳዳት በመከባበርና በአብሮነት ሊሆን እንደሚገባ ገልፀዋል።

በዓሉ ከኢትዮጵያ ባሻገር በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ በመሆኑ የሃገራችንን ባህልና ትውፊት ለማስተዋወቅ ትልቅ እገዛ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

 

የቅድስት ስላሴ ካቴድራል አገልጋይ የሆኑት መምህር በቃሉ ሞላ የበዓሉ አከባበር ከሃይማኖታዊ እሴቱም ባለፈ አብሮነትና መተባበር የሚታይበት የፍቅርና የአንድነት ማሳያ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም