ቀጥታ፡

የጥምቀት በዓል አብሮነትን እና አንድነትን ለማጠናከር ትልቅ ሚና አለው

አዲስ አበባ፤ጥር 11/2018 (ኢዜአ)፦የጥምቀት በዓል የህዝቦችን አብሮነትና አንድነት ለማጠናከር ትልቅ ሚና እንዳለው  የበዓሉ ታዳሚ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለፁ።

የጥምቀት በዓል በጃንሜዳ የሀይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ በርካታ ምዕመናን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በተገኙበት ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ የታደሙና አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የጥምቀት በዓል የህዝቦችን አብሮነትና መተሳሰብ ለማጠናከር የጎላ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወጣት ምህረት ታደለ እየሱስ ክርስቶስ ራሱን ዝቅ አድርጎ ትህትናን ሲያስተምር ሰዎች እርስ በእርሳቸው እንዲከባበሩና እንዲዋደዱ ትምህርት የሚሰጥ ነው ስትል ተናግራለች።  


 

በዚህም ምዕመኑ በዓሉን ሲያከብር አቅም የሌላቸውን ዜጎች በመርዳት እና በማካፈል አብሮነቱን እና አጋርነቱን በሚያሳይ መልኩ መሆን እንዳለበት ጠቁማለች።

በዓሉ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም በማይዳሰስ ቅርስም መመዝገቡ የኢትዮጵያን ባህልና ትውፊት ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝም ጠቅሳለች።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ፋሲል ሃይሌ በበኩላቸው የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ አስተምህሮው በተጨማሪ በህዝቦች መካከል ፍቅር፣አንድነትና የመተሳሰብ ባህልን ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።


 

በዓሉ በማይዳሰስ ቅርስም የተመዘገበ በመሆኑ የበለጠ ለዓለም ህዝብ ሃገራችንን ለማስተዋወቅና የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ጠቅሰዋል።

በዓሉን ከአካባቢው ነዋሪዎች ባለፈ ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ እንግዶች መታደማቸውን ገልፀው፤ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ አግባብ መከበሩን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ሃይለጊዮርጊስ ክፍሌ ናቸው።


 

 

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ሙሉ ታደለ በተለይም በጃንሜዳ የተከበረው የጥምቀት በዓል ትንሽ ትልቅ ሳይል ሁሉንም የእምነቱ ተከታዮች ባሳተፈ መልኩ መከበሩ ደስ እንዳሰኛቸው ተናግረዋል።


 

በዓሉ ኢትዮጵያውያን ወንድማማችነትንና አንድነትን ለዓለም የምናሳይበት አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ሲሉ ገልፀዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም