በጥምቀት በዓል ላይ የሚታየው ስነ-ስርዓት፣ ውበትና ድምቀት አስደናቂ ነው- የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች - ኢዜአ አማርኛ
በጥምቀት በዓል ላይ የሚታየው ስነ-ስርዓት፣ ውበትና ድምቀት አስደናቂ ነው- የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች
አዲስ አበባ፤ጥር 11/2018 (ኢዜአ)፦በጥምቀት በዓል ላይ የሚታየው ስነ-ስርዓት፣ ውበትና ድምቀት አስደናቂ መሆኑን በአዲስ አበባ የጥምቀት በዓል ላይ የተገኙ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ተናገሩ።
የጥምቀት በዓል በጃንሜዳ የሀይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ በርካታ ምዕመናን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ የታደሙና አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች በመዲናዋ የጥምቀት በዓል አከባበር፣ በሕዝቡ ባህል፣ የሃይማኖት መከባበር እንዲሁም በከተማው ልማትና ውበት መደነቃቸውን ተናግረዋል።
ከአሜሪካ በዓሉን ለመታደም ለመጀመሪያ ጊዜ የመጡት ሊያ ሮዝ በበዓሉ አከባበር ስነ-ስርዓትና ድምቀት መደነቃቸውን ገልጸዋል።
የጥምቀት በዓልን ለማክበር በርካታ ቁጥር ያለው ህዝብ ተሳትፎ ያለምንም ችግር በሰላም ተመልሶ መግባቱ በጣም የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።
በመዲናዋ በተመለከቱት ልማትና ውበት ፣ አረንጓዴና ውብ ስፍራዎች፣ የአየር ሁኔታ እንዲሁም የሰዎች እንግዳ አቀባበል አስደሳች መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ከሩቅ ሆነን የሰማነው እና አሁን በአካል መጥተን ስናየው በጣም የተለየ ነው ብለዋል።
ሌላው አሜሪካዊ ደስቲን ፔንራድ በበዓሉ ላይ በመገኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በጣም ልዩና ልትጎበኝ የምትገባ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
በጉብኝታቸው ኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይና የበለጸገ ባህል እንዳላቸው መመልከታቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በጣም የበለፀገ ባህል አላት ይህን እምቅ ሀብት ሌሎች ጎብኝዎች መጥተው እንዲመለከቱ እንደሚመክሩ ገልጸው እሳቸውም በድጋሚ መጥተው እንደሚጎበኙ ተናግረዋል።
ከደቡብ ኮርያ የመጡት ሱጅን ፓርክ በጥምቀት በዓል ስነ-ስርዓት መደሰታቸውንና መደነቃቸውን ገልጸው፤ በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት ፍላጎት እንዳላችውም ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ የነጻነትና የአንድነት ከተማ መሆኗን ለማየት ችለናል ሲሉም ተናግረዋል።