ቀጥታ፡

የጥምቀት በዓል ከኃይማኖታዊ ይዘቱ  ባሻገር የአንድነትና የመተሳሰብ መገለጫ ነው

አዲስ አበባ፤ጥር 11/2018 (ኢዜአ)፦የጥምቀት በዓል ከኃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር የአንድነትና የመተሳሰብ መገለጫ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ አስገነዘቡ።

የጥምቀት በዓል የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣የተለያዩ  አገራት አምባሳደሮች፣ በርካታ ምዕመናን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችና የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች በተገኙበት በጃን ሜዳ በድምቀት ተከብሯል።


 

የቅዱስነታቸውን መልዕክት ያቀረቡት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ፣ ለሀገራዊ አንድነትና ማህበራዊ ትስስር መጎልበት በጋራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሰላምን ማጽናትና አብሮነትን ማጠናከር የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት መሆኑን የጠቀሱት አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ የሀገርን ልማት ለማረጋገጥ በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።


 

በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን እና አባቶች ጠብቀው ያቆዩትን ይህን ታላቅ በዓል የአሁኑ ትውልድም የማጠናከርና የመጠበቅ አደራ እንዳለበት ገልጸዋል።


 

የጥምቀት በዓል የእምነት መግለጫ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን የአንድነት፣ የመፈቃቀርና የጨዋነት መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ በመጠመቅ የሰውን ልጅ ከኃጢዓት እንዳነጻ ሁሉ፣ ምዕመናንም የጥምቀቱን መንፈሳዊ ዓላማ በመረዳት በእለት ተእለት ሕይወታቸው ሊተረጉሙት ይገባል ሲሉ  ገልጸዋል። 

ቤተክርስቲያኗ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች ተጠብቀው እንዲቆዩ የድርሻዋን መወጣቷንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም