ቀጥታ፡

የጥምቀት በዓል ትህትናን እና እርስ በእርስ መከባበርን የሚያስተምር  ነው

አዲስ አበባ፤ጥር 11/2018 (ኢዜአ)፦የጥምቀት በዓል ለሰው ልጆች ትህትናን እርስ በእርስ መከባበር እና ምህረትን የሚያስተምር ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሃዋሪያት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አባ ጴጥሮስ በርጋ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጥምቀት በዓልን በልደታ ማርያም ካቶሊክ ካቴድራል በተለያዩ ስነ ስርዓቶች አክብራለች።


 

በስነ ስርዓቱ  ላይ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሃዋሪያት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አባ ጴጥሮስ በርጋ እንደገለጹት፤የጥምቀት በዓል  በዓለም ላይ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ሁሉ ታላቅ በዓል ነው።

የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ ትህትናን፣ እርስ በእርስ መከባበርን መዋደድ እና ምህረትን ያስተማረበት መሆኑን ተናግረዋል።


 

በመሆኑም ምዕመኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ትህትና እርስ በእርስ መከባበርን በአርአያነት መውሰድ እንደሚገባው ገልጸዋል።

የልደታ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ታሪኩ ዝናቡ በበኩላቸው፤ የጥምቀት በዓል አንድነትና  አብሮነትን የሚያጎላ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ይህን አንድነት የሁል ጊዜ ተግባር በማድረግ ሰላምና ፍቅርን  ለትውልድ  ማስተላለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

በአከባበር ሥነ ሥርዓቱ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሙሉ ታደሰ እንደገለጹት፤ የጥምቀት በዓል በሰላምና በፍቅር በአንድነት የሚከበር ከሌሎች በዓሎች የተለየ ስሜት ያለው ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም