ቀጥታ፡

የኮሪደር ልማት የስራ ባህልን ከመለወጥ አልፎ አዲስ አበባን የቱሪዝም ማዕከል የማድረጉን እንቅስቃሴ ውጤታማ አድርጓል

አዲስ አበባ፣ጥር 11/2018 (ኢዜአ) ፦የኮሪደር ልማት የስራ ባህል እንዲለወጥ ከማድረግ ባሻገር አዲስ አበባን የቱሪዝም ማዕከል የማድረጉ እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ በመዲናዋ የኮሪደር ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ እየተሳተፉ ላሉ ሰራተኞች ማዕድ አጋርተዋል።  


 

ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የኮሪደር ልማት የአዲስ አበባን ገጽታ በመቀየር አዲስ አበባን የቱሪዝም ማዕከል የማድረጉ ስራ ውጤታማ እንዲሆን አዎንታዊ አስተዋፅኦ እያበረከት ነው። 

የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ውብ፣ጸዱና ለነዋሪዎች ምቹ  ከማድረግ ባለፈ የስራ ባህል እንዲቀየር መሰረት እየጣለ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

በኮሪደር ልማት ላይ የተሳተፋችሁ ባለሙያዎች እና ሰራተኞች የዚህ ውጤት ምክንያት ናችሁ፤ ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ ያመሰግናችኋል ብለዋል። 

በተለወጠ የስራ ባህል የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ስራዎች ገቢራዊ ማድረግ የትኩረት ማዕከላችን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም