ቀጥታ፡

ጥምቀትን የመደጋገፍ ባህልን በማጎልበት ማክበር ይገባል - አቡነ በርቶሎሜዎስ 

ድሬዳዋ፣ጥር 11/2018 (ኢዜአ) ፦ የጥምቀት በአልን ኃይማኖታዊ እሴቱን በመጠበቅና የመደጋገፍ ባሀልን በማጎልበት ማክበር እንደሚገባ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ በርቶሎሜዎስ ተናገሩ።

 የጥምቀት በአል በተለያዩ ኃይማኖታዊ ስርአቶች በደመቀ መንገድ በድሬዳዋ እየተከበረ ነው።

የድሬደዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ በርቶሎሚዎስ በባህረ ጥምቀት ለተሰበሰበው የበዓሉ ታዳሚ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።


 

ብፁዕ አቡነ በርቶሎሜዎስ በወቅቱ  በአሉ የሰላም፣ የደስታ፣ የፍቅርና የአብሮነት እንዲሆን ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

በአሉን ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳትና በመደገፍ፣ የታመሙትን በመጠየቅና በመንከባከብ መሆን አለበትም ብለዋል።

ብፁዕነታቸው አክለውም የጥምቀት በአልን ስናከብር ኃይማኖታዊ እሴቶችን በመጠበቅ፤ የአብሮነትና የመደጋገፍ ባህላችንን በሚያጎለብት መንገድ መሆን ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።


 

በስፍራው የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይና የከንቲባው ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገበየሁ ጥላሁን በበኩላቸው፤ ለመላው የበዓሉ ታዳሚ የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

 በአሉን የእርስ በእርስ መረዳዳትና መደጋገፍ እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር ማክበር ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

ትህትናና መከባበር የህይወታችን መርህ መሆን እንዳለበትም አቶ ገበየሁ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም