ቀጥታ፡

የጥምቀት በዓል የሰው ልጅ ነፃነትና ፍቅር የታወጀበት በዓል ነው - አቡነ በርናባስ

ሰቆጣ ፣ጥር 11/2018 (ኢዜአ) ፦የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ ነፃነትና ፍቅርን ያወጀበት በዓል ነው ሲሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የዋግ ኽምራ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ በርናባስ ገለፁ።

የጥምቀት በዓል በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።


 

የዋግ ኽምራ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርናባስ ለበዓሉ ታዳሚ እንዳሉት የጥምቀት በዓል የሰው ልጅ በበደሉ ከነበረበት ጨለማ ወደ ብርሃን የተሸጋገረበት ታላቅ በዓል ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ በአካል ተገልጦ በዮሐንስ እጅ በመጠመቅ ምስጢሩን የገለጠበት፤ የሰው ልጅ ነፃነትና ፍቅር የታወጀበት በዓል ነው ሲሉ  ተናግረዋል።

ምእመኑም የበዓሉን ሃይማኖታዊ አስተምህሮንና ተምሳሌትነቱን የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ በተግባር መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በበዓሉ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ ምእመናንና የብሄረሰብ አስተዳደሩና የሰቆጣ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም