ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል አከባበር ልዩና ድንቅ ስርአት ያለው ነው

አርባምንጭ፤ጥር 11/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል አከባበር ልዩና ድንቅ ስርአት ያለው መሆኑን በአርባምንጭ በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ገለጹ።

የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ፣የአባያና ጫሞ ሀይቆች፣ የ40ዎቹ ምንጮች፣ የአዞ ራንች፣ የባህላዊ የሸማ እና ጎጆ ቤት ጥበብ እና የሌሎች መስህቦች መገኛ የሆነችው አርባምንጭ ከተማ ዓመቱን ሙሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ጎብኚ ታስተናግዳለች።

ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ጎብኚዎች የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል ከአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ጋር እያከበሩ ይገኛሉ።

ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስተያየታቸውን የሰጡ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች እንደተናገሩት የኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል አከባበር ልዩና ድንቅ ስርአት ያለው ነው፡፡

የጥምቀት በዓልን ከኢትዮጵያዊያን ጋር በማክበራችን ልዩ ደስታና የማይረሳ ትዝታ ፈጥሮልናል ብለዋል።


 

ፖላንዳዊው ጎብኚ ጃክ ቶርብሊዝ ኢትዮጵያዊያን የሚያከብሩትን የጥምቀት በዓል መመልከት በመቻሉ እጅግ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ስርዓቱና አከባበሩ ልዩና የትም የሌለ ድንቅ በዓል ነው ሲል ገልጿል።

የዓለም ቅርስ የሆነው ኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል ስርአት ተጠብቆ ለትውልድ ሊተላለፍ የሚገባ ነው ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ የሰላም ምድር ናት ያለው ጎብኚው ሀገሪቱ በሁሉም ዘርፍ በፈጣን ዕድገት ላይ መሆኗን መመልከቱንም ነው የገለጸው።

በዓለም ባሉ ከአንድ መቶ በላይ ሃገራት መዘዋወራቸውን የገለጹት ፊንላንዳዊቷ ኢቫ ፓሎጃርቢ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያዊያን የጥምቀት በዓል ልዩና ድንቅ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ሁሉም በነጭ አለባበስ ደምቀው በአንድነት፣ በዝማሬና በቅዳሴ የሚፈጽሙት ሃይማኖታዊው ስርአት በጣም ደስ የሚያሰኝ ነው ብለዋል።

የስነ ጽሑፍ ባለሙያ መሆናቸውን የገለጹት ጎብኚዋ ስለ ኢትዮጵያ ቅርስና ባህል በመጻፍ ለሌሎች እንደሚያስተዋውቁ ተናግረዋል።

ሜክስኳዊው ካርሎስ ጎሚክሎጋ በበኩሉ፥ የጥምቀት በዓልን ጨምሮ የመስህብ ስፍራዎችን ለመመልከት ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን ገልጿል።


 

ልዩ የሆነውን የጥምቀት በዓል ኢትዮጵያ ውስጥ በማክበሩ ደስተኛ መሆኑን ገልጾ፥ እንግዳ አክባሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ባሳዩኝ ፍቅር እና አክብሮት ደስ ተሰኝቻለሁ ብሏል።

ወደ ሀገሬ ስመለስ ሌሎች ጓደኞቼ የኢትዮጵያን ቅርስ፣የመስህብ ስፍራዎችና በዓላትን እንዲጎበኙ እነግራቸዋለሁ ብሏል።

በዓለም የማይደሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል በመላ ሃገሪቱ በሃይማኖታዊ ስርዓት በድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም