ቀጥታ፡

አዲስ አበባ ውብና ፅዱ መሆኗ ለአደባባይ በዓላትና ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ጥር 11/2018 (ኢዜአ) ፦አዲስ አበባ ውብና ፅዱ መሆኗ በአደባባይ ለሚከበሩ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ከጊዜ ወደ ጊዜ የቱሪስት ቁጥር እንዲጨምር ማስቻሉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት እየተከበረ በሚገኘው የጥምቀት ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በጥምቀት በዓል ወቅት የኢትዮጵያ ህብረ-ቀለም በጉልህ የሚታይበት ነው ብለዋል።

የጥምቀት በዓል የዳግም ልደትና የመገለጥ ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዓሉን ስናከብር አንድነትን፣አብሮነትን እና ህብረ-ብሔራዊ መተሳሰብን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባም አንስተዋል።


 

ከተማዋ ጸድታና ደምቃ መታየቷ ለቱሪስቶች ሳቢነቷን እንደጨመረው የገለጹት ከንቲባዋ፣ ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት መቻሉ ለከተማዋ የልማት ስራዎች መሳለጥ ትልቅ አቅም መሆኑን ጠቁመዋል።

የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ ከተመዘገበ ወዲህ የዓለምን ዓይን ወደ ኢትዮጵያ በመሳብ በየዓመቱ የበርካታ ጎብኚዎች መዳረሻ እየሆነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በበዓል አከባበሩ ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና ሌሎችም ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም