ሃይማኖታዊ፣ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች የሕብረ-ብሔራዊ ትስስር ማጠናከሪያ ናቸው- ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ - ኢዜአ አማርኛ
ሃይማኖታዊ፣ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች የሕብረ-ብሔራዊ ትስስር ማጠናከሪያ ናቸው- ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ
አዲስ አበባ፣ጥር 11/2018 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያውያን ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች የሕብረ-ብሔራዊ ትስስር ማጠናከሪያና የኢትዮጵያ ከፍታ የሚታይባቸው መሆናቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለፁ።
በጃን ሜዳ በድምቀት እየተከበረ በሚገኘው የጥምቀት በዓል ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣በርካታ ምዕመናን፣የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ተገኝተዋል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የኢትዮጵያውያን ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች የሕብረ-ብሔራዊ ትስስር ማጠናከሪያና የኢትዮጵያ ከፍታ መገለጫዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በብዝኃ ማንነት፣ በሃይማኖትና በተለያዩ ባህላዊ መገለጫዎች ያሸበረቀች የሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ተምሳሌት ናት ብለዋል።
የኢትዮጵያውያን ሕብረ-ብሔራዊ ጌጦች የአንድነታችን መገለጫዎች ናቸው ያሉት ሚኒስትር ሸዊት፥ የሀገርን ሉዓላዊነት የሚፈታተኑ ጉዳዮች ሲገጥሙ ሕዝቡ በአንድነት እንዲቆም የሚያደርጉት እነዚህ የጋራ እሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የጥምቀት በዓል ከሀገር አልፎ የዓለም ቅርስ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የበርካታ ጎብኝዎችን ቀልብ መሳቡንም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበዓሉን ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ጠብቆ እንዲቆይ ላደረገችው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በዓሉ ሲከበር ለሀገሪቱ ሰላምና ብልጽግና በጋራ ለመሥራት ቃል በመግባት መሆን እንዳለበት ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል።