የጎንደር ከተማ ቀደምት የሥልጣኔ አብሪ ኮከብነቷን በማደስ ላይ ትገኛለች -ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የጎንደር ከተማ ቀደምት የሥልጣኔ አብሪ ኮከብነቷን በማደስ ላይ ትገኛለች -ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ጥር 11/2018 (ኢዜአ) ፦ጎንደር በመካከለኛ ዘመን ያጋጠማትን የጉስቁልና ስብራት በማራገፍ ቀደምት የሥልጣኔ አብሪ ኮከብነቷን በማደስ ላይ እንደምትገኝ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
በታሪካዊቷ ጎንደር የፋሲለደስ ጥምቀተ ባሕር የጥምቀት በዓል ኃይማኖታዊ ትውፊትና ሥርዓቱን ጠብቆ በታላቅ ድምቀት በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በአከባበር ሥነ-ስርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
የጥምቀት በዓል ለጎንደር እና አካባቢው ማህበረሰብ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ዕድገት በማሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ጎንደር በልዩ ሁኔታ የምታከብረው የጥምቀት በዓልም ሥርዓቱን በጠበቀ መንገድ አክብሮ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የጎንደር የመታደስ ጊዜ መጥቷል ያሉት ርዕሰ መሥተዳደሩ፥ ጎንደር በመካከለኛው ዘመን ያጋጠማትን ጉስቁልና በማራገፍ ቀደምት የሥልጣኔ አብሪ ኮከብነቷን በማደስ ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡
የከተማዋ የመታደስ ዘመንም ዕድገቷን በማፋጠን ከተማዋን ለነዋሪዎችና ጎብኝዎቿ ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የጎንደር ሕዝብና ወዳጆች ከተማዋን ለማልማት በሚደረገው ጥረት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፥ የዘመናዊቷ ከተማ መሥራች አጼ ፋሲለደስ ያስገነቡት የመጠመቂያ ገንዳ ጥምቀትን በጎንደር ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
ጥምቀት በጎንደር ሥርዓቱን በቃል ለመግለጽ በማይቻል ድምቀት የሚከበር ኃይማኖታዊ እሴት መሆኑን ገልጸዋል።
በጥምቀት በዓል መለያየትን በአንድነት፣ ጥልን በፍቅር፣ መፍረስን በመገንባት፣ ጨለማን በብርሃን፣ ድህነትን በብልጽግና ድል መንሳት እንደሚገባም ተናግረዋል።