ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የታሪክ ከፍታና የቤተክርስቲያን አስተምህሮ መስፋፋት የጎንደር ሚና ታላቅ ነው- ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ

አዲስ አበባ፣ጥር 11/2018 (ኢዜአ) ፦በኢትዮጵያ የታሪክ ከፍታና የቤተክርስቲያን አስተምህሮ መስፋፋት የጎንደር ሚና ታላቅ መሆኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ-ክህነት ሥራ አስኪያጅ እና የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ገለጹ።

በታሪካዊቷ ጎንደር የፋሲለደስ ጥምቀተ ባሕር የጥምቀት በዓል ኃይማኖታዊ ትውፊትና ሥርዓቱን ጠብቆ በታላቅ ድምቀት በመከበር ላይ ይገኛል።


 

በአከባበር ሥነ-ስርዓቱ ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ-ክህነት ሥራ አስኪያጅ እና የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በመልዕክታቸው፥ ጥምቀት የመለገጥ በዓል ነው ብለዋል።

ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ በዮሐንስ እጅ በመጠመቅ ትልቅ ትህትናን በመግለጥ የዕዳ ደብዳቤ የተቀደደበት በዓል ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ከጌታችን ሞትና ትንሳኤ ጋር በታላቅ ድምቀት የጥምቀት በዓል የሚከበርባት ጎንደር በታሪካዊ ቅብብሎሽ ሀገር የተገነቡ የታላላቅ ነገሥታት ከተማ ናትም ብለዋል።

ለዚህም ጎንደር የሀገር ጥበብ መሆኗን ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናትና ቅርሶች ህያው ምስክር መሆናቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የከፍታ ታሪክና የቤተክርስቲያን አስተምህሮ መስፋፋት የጎንደር ሚና ታላቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ታሪካዊና መንፈሳዊ ቅርሶችን በመጠበቅ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


 

ኢትዮጵያ ወደ ታሪካዊ የዕድገት ማማ ለመሻገር በምታደርገው ጥረት ሊቃውንት ሚናቸውን ማስቀጠል እንደሚጠበቅባቸውም ጠቅሰዋል።

በአከባበር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ተገኝተዋል።

እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትና በርካታ የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች በተገኙበት በፋሲለደስ ባሕረ ጥምቀት በታላቅ ድምቀት በተለያዩ ኃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም