በዓሉ ሲከበር የተቸገሩትን በመርዳት፣ የተራቡትን በማብላት እና የታመሙትን በመጠየቅ ሊሆን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በዓሉ ሲከበር የተቸገሩትን በመርዳት፣ የተራቡትን በማብላት እና የታመሙትን በመጠየቅ ሊሆን ይገባል
አዳማ፣ጥር 11/2018 (ኢዜአ) ፦ጥምቀት የበረከት በዓል በመሆኑ በዓሉን ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳት፣ የተራቡትን በማብላት እና የታመሙትን በመጠየቅ ሊሆን ይገባል ሲሉ ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ ገለጹ።
የጥምቀት በዓል በአዳማ መስቀል አደባባይ በሚገኘው ባህረ ጥምቀት በደማቅ ሥነ ሥርዓት እየተከበረ ነው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት፤ በዓሉን በመረዳዳት እና በመተጋገዝ ማሳለፍ ይገባል።
ጥምቀት የበረከት፣ የነፃነትና የይቅርታ ቀን መሆኑን ጠቅሰው ይህንን እሴት በመመርኮዝ ቤተክርስቲያን መልካም ስራን ታውጅበታለች ብለዋል።
በመሆኑም በዓሉን ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳት፣ የተራቡትን በማብላት እና የታመሙትን በመጠየቅ ሊሆን ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
የጥምቀት በዓል ከኃይማኖታዊ ትውፊቱ ባሻገር ባህላዊ መገለጫም ያለው በመሆኑ ምዕመኑ በዓሉን እሴቱን በጠበቀ መልኩ ማክበር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።