የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ እሴቱ ባለፈ የህዝቦችን አብሮነትና አንድነት ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ እሴቱ ባለፈ የህዝቦችን አብሮነትና አንድነት ያጠናክራል
ጋምቤላ፤ጥር 11/2018 (ኢዜአ)፦ የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ እሴቱ ባለፈ የህዝቦችን አብሮነትና አንድነት በማጠናከር ረገድ የጎላ ፋይዳ ያለው መሆኑን በጋምቤላ ከተማ የበዓሉ ታዳሚዎች ገለጹ።
በጋምቤላ ከተማና አካባቢው የጥምቅት በዓል ኃይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት እየተከበረ ነው።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል አቶ ፍስሃ ጌታቸው በሰጡት አስተያየት፥ የጥምቀት በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በአብሮነትና በአንድነት የሚከበር ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም በዓሉን እርስ በርስ በመደጋገፍና በመተባበር በጋራ እያከበሩት እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በጋምቤላ ከተማና አካባቢው የጥምቀት በዓል በልዩ ድምቀትና ድባብ በየዓመቱ እየተከበረ ያለ ሃይማኖታዊ በዓል መሆኑን የገለጸችው ደግሞ ሌላዋ የበዓሉ ታዳሚ ወጣት ናርዶስ አቦወርቅ ናት።
በዓሉ ከሃይማኖታዊ ትውፊቱ ባለፈ የህዝቦችን አብሮነት፣ አንድነትና ህብረትን እያጠናከረ የሚገኝ ክብረ በዓል መሆኑን ተናግራለች።
ሌላው የበዓሉ ታዳሚ አቶ ግርማይ መሃሪ በሰጡት አስተያየት፥ የጥምቀት በዓል በየዓመቱ በጉጉት ከሚጠበቁ ታላላቅ ዓመታዊ ክብረ በዓላት መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓሉ በድምቀት ከሚከበሩባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከል ጋምቤላ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዓሉ በተለይም ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ደምቀው የሚታዩበት በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለት የኪዳነ ምህረት፣ የቅዱስ ገብርኤልና ሌሎች ታቦታት ከጥምቀተ ባህሩ ወደ መንበረ ክብራቸው በምዕመናን ታጅበው ይሸኛሉ።