የኢትዮጵያውያንን እውነትን ወዳድነት፣ ትዕግስት፣ አስተዋይና የጀግንነት ባህሪ በአርቆ አሳቢነት መንገድ አፅንቶ ማስቀጠል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያውያንን እውነትን ወዳድነት፣ ትዕግስት፣ አስተዋይና የጀግንነት ባህሪ በአርቆ አሳቢነት መንገድ አፅንቶ ማስቀጠል ይገባል
አዲስ አበባ፣ጥር 11/2018 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያውያንን እውነትን ወዳድነት፣ ትዕግስት፣ አስተዋይና የጀግንነት ባህሪ በአርቆ አሳቢነት መንገድ አፅንቶ ማስቀጠል እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
በታሪካዊቷ ጎንደር የፋሲለደስ ጥምቀተ ባሕር የጥምቀት በዓል ኃይማኖታዊ ትውፊትና ሥርዓቱን ጠብቆ በታላቅ ድምቀት በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በአከባበር ሥነ-ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ጎንደርን ከሚያደምቁ ዐበይት መንፈሳዊና ኃይማኖታዊ በዓላት መካከል ጥምቀት ግንባር ቀደሙ ነው ብለዋል።
የጎንደር የኪነ-ሕንፃ የጥበብ አሻራም የሚታይና የሚዳሰስ ታሪካዊ ፀጋ መሆኑን ገልጸዋል።
የጎንደር ህዝብ እንደሌሎች ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለሰው ልጅ የላቀ ክብርና ፍቅር ያለው እንደሆነም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያዊነት መገለጫው ስክነትና አስተውሎት ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ታዬ፣ ይህን የብልህ መንገድም መከተል ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያውያንን እውነትን ወዳድነት፣ ትዕግስት፣ አስተዋይና የጀግንነት ባህሪ በአርቆ አሳቢነት መንገድ አፅንቶ ማስቀጠል እንደሚገባ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ጉዞ በፍጥነት ከሚገሰግሱና ከሚራመዱት ጋር መሆን እንደሚኖርበትም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በተለዋዋጭ የዓለም አቀፍ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያውያን አርቆ ማስተዋልና በተረጋጋ ሁኔታ መመልከት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።
በአንድ ዓመት ውስጥ ያየሁት ለውጥ አስደናቂ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ሀሳብ ትውልድና አመራር ሲስማማ ታሪክ መሥራት እንደሚቻል ጎንደር ማሳያ ናት ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የጎንደር ከተማን ዳግም ውልደት በተግባራቸው ለዋጁ አካላት ሁሉ ፕሬዝዳንቱ ምስጋና አቅርበዋል።
ትጉህ ልጆች ካሉ ተስፈንጥሮ መሄድ እንደሚቻል በጎንደር በተጨባጭ መታየቱን ገልፀው፣ ሀሳባችን ታፍራና ተከብራ የምትኖረውን ኢትዮጵያ ማፅናት ነው ብለዋል።
የጎንደር ከተማ የደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተክርስቲያን እርጅና በማደስ ወደ ድሮ ወጉና ማዕረጉ ለመመለስ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በአከባበር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ተገኝተዋል።
እንዲሁም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ-ክህነት ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
በተጨማሪም የዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትና በርካታ የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች በተገኙበት በፋሲለደስ ባሕረ ጥምቀት በታላቅ ድምቀት በተለያዩ ኃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።