ቀጥታ፡

ሴኔጋል 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫን አነሳች

አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2018 (ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ሴኔጋል ሞሮኮን 1 ለ 0 አሸንፋለች።

ማምሻውን በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጨዋታው ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ብራሂም ዲያዝ በጭማሪ ሰዓት ላይ የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት አልተቀመበትም።

የፍጹም ቅጣት ምቱን ውሳኔ በመቃወም  የሴኔጋል ተጫዋቾች ሜዳ ለቀው በመውጣታቸው ጨዋታው ተቋርጦ ነበር።

የሴኔጋል ተጫዋቾች ተመልሰው ከገቡ በኋላ ጨዋታው የቀጠለ ሲሆን ዲያዝ በቄንጠኛ መንገድ (ፓኔካ) ፍጹም ቅጣት ምት ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ የሴኔጋል ኤድዋርድ ሜንዲ አድኖበታል።

ጨዋታው ወደ ጭማሪ ሰዓት አምርቷል።

ፓፕ ጌይ በ94ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ሴኔጋልን አሸናፊ አድርጋለች።

ውጤቱን ተከትሎ ሴኔጋል ለሁለተኛ ጊዜ የአፍሪካን ዋንጫን አንስታለች።

ሴኔጋል ከዋንጫው በተጨማሪ የወርቅ ሜዳሊያው እና የ10 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አግኝታለች። ሽልማቱ በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ትልቁ ነው።

ሴኔጋል እ.አ.አ በ2019 በግብጽ የተዘጋጀውን 32ኛ የአፍሪካ ዋንጫ ማንሳቷ የሚታወስ ነው።

አዘጋጇ ሞሮኮ ከ50 ዓመታት በኋላ የአፍሪካ ዋንጫ የማንሳት ህልም አልተሳካም።

ሞሮኮ ብቸኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ያነሳችው በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እ.አ.አ በ1976 በተካሄደው 10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነው።

ሞሮኮ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ በማጠናቀቅ የብር ሜዳሊያ እና የአራት ሚሊዮን ሽልማት አግኝታለች።

የአትላስ አንበሶች በውድድር ጨዋታዎች ከሁለት ዓመት በኋላ ተሸንፋለች።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ለውድድሩ ተሳታፊ ሀገራት የ32 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሽልማት አዘጋጅቷል።

ከፍጻሜው ጨዋታ በፊት ደማቅ የመዝጊያ ስነ ስርዓት ተደርጓል።

ከታህሳስ 12 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም