ቀጥታ፡

የጎንደር የቅርስ ጥበቃና የልማት ስኬቶች የከተማዋን ገናና የሥልጣኔ ዘመን ዳግም ያበሰሩ ናቸው - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2018 (ኢዜአ)፦የጎንደር የቅርስ ጥበቃና የልማት ስኬቶች የከተማዋን ገናና የሥልጣኔ ዘመን ዳግም ያበሰሩ መሆናቸውን ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።

ለጎንደር ከተማ ማንሠራራት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋና እና ዕውቅና መርሃ ግብር በዓፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥታት ቅጥር ግቢ ተካሂዷል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፤ ለጎንደር ከተማ ልማት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሁሉ የላቀ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

የጎንደር ሕዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት ካለው ቀናኢነትና ታታሪነት ባሻገር፣ ያደረጉለትን ማመስገን ባህሉ መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለዓፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥታት ዕድሳትና ለጎንደር ገናና የታሪክ ሥልጣኔ መነሳት ላበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።


 

በአሁኑ ወቅት ጎንደር በትውልድ ትንሣኤ ዘመን ላይ መሆኗን ገልጸው፤ የጎንደር ገናና የሥልጣኔ ታሪክ የኪነ-ጥበብ፣ የትምህርት፣ የዕድገትና የልማት መገለጫዋ ነው ብለዋል።

ይህ እንዲሆን በጎንደር ከተማ የልማትና የቅርስ ዕድሳት ስኬት ለተጨነቁና ላሰቡ፣ በትግበራ ሂደቱና በፍጻሜው ደስታን ላገኙ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በቀጣይም የጎንደርን ዕድገትና ብልጽግና በማስቀጠል፣ በቅርስ ጥበቃና አዳዲስ ልማትን በማንበር ሕዝብን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል።


 

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፤ "ጎንደር ትሞሸር" በሚል ለቀረበው ጥሪ ሁሉም በጎ ምላሽ በመስጠት ከተማዋ ውብና ምቹ እንድትሆን ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነዋል።

ጎንደርን ይበልጥ ውብ፣ ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ እና የቱሪስት መዳረሻነቷን ለማጠናከር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ዳግም ጥሪ አቅርበዋል።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው፤ በአሁን ወቅት የጎንደር የሥልጣኔ ዘመን በብልጽግና መንገድ እያንሠራራ ነው ብለዋል።


 

በጎንደር ዓፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥታት ዕድሳትና የልማት ስኬቶች ድጋፍና አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።


 

በዕውቅና መርሃ ግብሩ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም