በከተራ በዓል የታየውን አንድነትና አብሮነት በማጠናከር ዘላቂ ማድረግ ይገባል - ምዕመናን - ኢዜአ አማርኛ
በከተራ በዓል የታየውን አንድነትና አብሮነት በማጠናከር ዘላቂ ማድረግ ይገባል - ምዕመናን
አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2018 (ኢዜአ)፦በከተራ በዓል የታየውን አንድነትና አብሮነት በማጠናከር ለዘላቂ የሀገር ዕድገት መስራት እንደሚገባ በአዲስ አበባ ከተማ የከተራ በዓልን ለማክበር ጃንሜዳ የተገኙ ምዕመናን ገለጹ።
የከተራ በዓል በመላ ሀገሪቱ በታላቅ ድምቀት ተክብሯል፡፡
በጃንሜዳ ኢዜአ ያነጋገራቸው የበዓሉ ታዳሚዎች፤ በዓሉ የኢትዮጵያን ድንቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች በሚያንጸባርቅ መልኩ መከበሩ ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
በዓሉን ከቤተሰቦቻቸው ጋር በጃንሜዳ የታደሙት አቶ መለሰ መኮንን እንደገለጹት፤ የከተራ በዓል የሕዝቦችን አንድነትና አብሮነት በሚያጎላ መልኩ ተከብሯል፡፡
በበዓሉ የታየውን አብሮነትና ውበት ለሀገር ዘላቂ ልማት በማዋል የተጀመረው ሀገራዊ ብልጽግና ከዳር እንዲደርስ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
ወጣት መቅደስ አየለ በበኩሏ፤ ሃይማኖታዊ በዓሉ እሴቱን ጠብቆ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ ከወጣቶች ዘርፈ ብዙ ጥረት ይጠበቃል ብላለች፡፡
ወጣቶች ዛሬ የታውን አንድነትና ህብረት በማጠናከር ለሀገር ዕድገት በንቃት ሊሳተፉ እንደሚገባም አስረድታለች።
የበዓሉ ታዳሚ አቶ ሽመልስ በቀለ በበኩላቸው፤ የዓለም ቅርስ የሆነው የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ጠቁመዋል።
የበዓሉ እሴት ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ የመጠበቅና የመንከባከብ ግዴታ የሁሉም ዜጋ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ብርቱካን ታደግ ናቸው፡፡
የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ በየዓመቱ ጥር 11 ቀን በታላቅ ድምቀት የሚከበር ሲሆን፣ በዓሉ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (UNESCO) በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ይታወሳል።