ቀጥታ፡

የከተራና ጥምቀት በዓል የሰላም ምልክት ነው- ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ

ወልድያና ፤ ጥር 10/2018 (ኢዜአ)፦ የከተራና ጥምቀት በአል  የሰላም ምልክት ነው ሲሉ   የሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ የከሚሴ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ ገለፁ።

የወልድያና ሰቆጣ ከተሞች ምዕመናን በሃይማኖታዊ ህብረ ዝማሬ  ታቦታትን አጅበው  ወደ ማደሪያ ስፍራቸው በማድረስ የከተራ በዓልን በድምቀት አክብረዋል።


 

በወልድያ በተከበረው የከተራ በአል ላይ  ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ  ባስተላለፉት መልእክት ፤ የጥምቀት በዓልን ስናከብር እርስ በርስ  በመተሳሰብ መሆን አለበት ብለዋል።


 

ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመጣው ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ለማዳን በመሆኑ እኛም  ለሀገራችን ሰላም ልንሰራ  ይገባል ብለዋል። 

በዓሉ የሰላም ምልክት እንደመሆኑ  በመከባበርና በመተሳሰብ፣ የተራበውን በማብላት፣ ህሙማንን በመጠየቅና ስለ ሀገራችን ሠላም በመጸለይ ልናከብረው ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

የወልድያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል  ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ በበኩላቸው፤ የጥምቀት በዓልን ስናከብር የሁሉም ነገር መሰረት የሆነውን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የጀመርነውን ጥረት  በጋራ በማስቀጠል መሆን  አለበት  ሲሉ አስረድተዋል። 


 

ወልድያን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ባለው ስራ የጥምቀት በዓል የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አልጠራጠርም ያሉት ከንቲባው ለስኬቱ ሁላችንም ልንተባበር ይገባል ብለዋል።

በተያያዘ ዜና የዋግ ኽምራ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ በርናባስ ፤በሰቆጣ ከተማ በተከበረው በዓል ላይ እንደገለጹት የከተራና የጥምቀት በዓል  በአንድነትና በፍቅር የምናከብረው  ነው ብለዋል ።


 

ምእመናን በዓሉን  በፍቅርና በአንድነት  እንዳከበሩት ሁሉ በቀጣይም አብሮነትና መተሳሰብ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም