ቀጥታ፡

የጥምቀት በዓል ማህበራዊ መስተጋብር ፋይዳው የላቀ ነው - የበዓሉ ታዳሚዎች

አዳማ  ፤ ጥር 10/2018 (ኢዜአ)፦ የጥምቀት በዓል ከኃይማኖታዊ አስተምህሮው ባሻገር ያለው ማህበራዊ  መስተጋብርና ባህላዊ  ፋይዳው የላቀ መሆኑን በአዳማ ከተማ የበዓሉ ታዳሚ የኃይማኖት አባቶችና ምዕመናን ገለጹ።

በዓሉ ህዝበ ክርስቲያኑ  በድምቀት የሚያከብረው፣ አብሮነታቸውን የሚያሳዩበት እንዲሁም ኢትዮጵያዊ አንድነታቸውን የሚያንጸባርቁበት መሆኑንም ተናግረዋል።

በአዳማ የከተራ በዓል ላይ ያነጋገርናቸው የአዳማ ደብረይድረስ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ መላከ ህይወት ቀሲስ ሀይለማርያም እንዳሉት፤ ጥምቀት ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ ድረስ በልዩ ኃይማኖታዊ አስተምህሮና መንፈሳዊ ክዋኔ የሚከበር ታላቅ  በዓል ነው።

የጥምቀት በዓል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱ ተጠምቆ አርአያ የሆነበት እና መለኮት የተገለጠበት ነው ሲሉም  አስረድተዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ የተጠመቀበት ምስጢር ዋና ዓላማው ለሰው ልጆች ትህትናን ለማስተማር በመሆኑ ትህትናን የእለት ተእለት መመሪያችን ልናደርገው ይገባል ብለዋል።

በዓሉ ከሀይማኖታዊ አስተምህሮው ባለፈም ማህበራዊ መስተጋብሩ እና ባህላዊ ፋይዳው የላቀ በመሆኑ  ሁሌም በልጅ አዋቂ ተናፋቂና ተወዳጅ  በዓል ሆኖ መዝለቁን  ነው ያስረዱት።


 

ጥምቀት ለዘመናት አሻግሮ ከዚህ ያደረሰን የአብሮ መኖር እሴታችንና እምነታችን በመሆኑ መጠበቅና መንከባከብ ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ ሌላው የበአሉ ታዳሚ አቶ ወንዱ ጥላሁን ናቸው።

በተለይም በጥምቀት በዓል የሚታየው  የሰዎች ፍቅር፣ መተሳሰብና የመተጋገዝ  መንፈስ ቀልብን የሚገዛ ስለሆነ ይበልጥ ለማጠናከር መትጋት ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል።


 

ሌላኛዋ የበአሉ ታዳሚ መሰረት ግርማ ፤   የከተራ በዓል ድባብ ሁሌም  ልዩ ደስታ ስለሚሰጣት  በናፍቆት እንደምትጠብቀው አመልክታለች።

በአዳማ በተከበረው የከተራ በዓል ላይ የምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ ካህናትና ሊቃውንት እንዲሁም መዘምራንና በርካታ ምእመናን ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም