የጥምቀት በዓል ፍፁም ትህትና እና ፍቅር የተገለጠበት ታላቅ በዓል ነው - ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ - ኢዜአ አማርኛ
የጥምቀት በዓል ፍፁም ትህትና እና ፍቅር የተገለጠበት ታላቅ በዓል ነው - ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ
ጂንካ፤ ጥር 10/2018 (ኢዜአ)፦ የጥምቀት በዓል በሰው ልጆች ዘንድ ሰላም የሰፈነበት፣ ፍፁም ትህትና እና ፍቅር የተገለጠበት ታላቅ በዓል ነው ሲሉ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ ገለጹ፡፡
የከተራ በዓል በጂንካ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
ታቦታቱም በምዕመናን እና በቀሳውስት ወረብና ዝማሬ ታጅበው በጥምቀተ-ባህር በተዘጋጀላቸው ማረፊያ ስፍራ ደርሰዋል።
የደቡብ ኦሞ እና የአሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ እና የቅድስት ስላሴ ካቴድራል ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ በክብረ በዓሉ ላይ ለምዕመኑ ቡራኬና መልዕክት አስተላልፈዋል።
ብፁዕነታቸው በዚሁ ወቅት የጥምቀት በዓል ፍፁም ትህትና የተማርንበት፤ ፍቅርና አንድነት የተገለጠበትና ሰላም የሰፈነበት ታላቅ ክብረ በዓል ነው ሲሉ አንስተዋል።
እኛም ከብረሃነ-ጥምቀቱ በተማርነው መሰረት መተሳሰብ፣ ፍቅርና አንድነትን መገለጫችን እና የሰርክ ተግባራችን ልናደርግ ይገባል ያሉት ብፁዕነታቸው፥ ከምንም በላይ ሰላማችንን መጠበቅ ይኖርብናል ብለዋል።
ምግባራችንን በማቅናት ቀናኢ ልብ እንዲኖረን መትጋት ይኖርብናል ያሉት ብፁዕነታቸው ፥ ይቅር ባይና ትሁት ልንሆን ይገባልም ብለዋል።
በተለይም ሀሜት፣ ውሸትና እኩይ ምግባርን በማስወገድ ፍቅርና አንድነትን ማስቀደም እንደሚገባም አሳስበዋል።
በጂንካ ከተማ የከተራ በዓል በደመቀ መልኩ ተከብሮ ውሏል።