ቀጥታ፡

የጥምቀት ከተራ በዓል ኃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓቶች መንፈስን የሚያድሱና አስደናቂ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2018 (ኢዜአ)፦‎ የጥምቀት ከተራ በዓል ኃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓቶች መንፈስን የሚያድሱና አስደናቂ መሆናቸውን የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ገለጹ።

ታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ፣ የጥምቀት ከተራ በዓል ሃይማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ይገኛል። 

በከተራ በዓሉ ላይ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎችና የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት ታቦታት በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ታጅበው ባሕረ ጥምቀት ደርሰዋል። 

በበዓሉ ላይ የታደሙ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎችም የበዓሉ ሥነ ስርዓት መንፈስን የሚያድስና እጅግ አስደናቂ መሆኑን ገልጸዋል።

በጎንደር ከተማ የከተራ በዓል የታደሙ የዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በበዓሉ ላይ ባዩት ሃይማኖታዊ ሥነ ስርዓት መደነቃቸውን ተናግረዋል፡፡


 

ከጎብኚዎቹ መካከል ፕሮፌሰር ፊሊፕ ቡሼ እንደተናገሩት፤ የጥምቀት በዓል ኢትዮጵያውያን በአብሮነት የሚያከብሩት ጥልቅ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ሥርዓት መሆኑን ተገንዝበዋል።

ምዕመናኑ በኅብረ ቀለምና በዜማ ታጅበው በዓሉን ሲያከብሩ ማየት መንፈስን የሚያድስ ልዩ ስሜት እንዳለው ገልጸው፤ የጥምቀት በዓል መላው የዓለም ሕዝብ ሊጎበኘው የሚገባ መንፈሳዊ ሥርዓት መሆኑን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።


 

ሌላኛው ጎብኚ ፍራንሲሶ ላቫሎው በበኩላቸው፤ በበዓሉ ላይ በመታደማቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው፣ በዓሉ ከኢትዮጵያውያን ጋር ጥብቅ ታሪካዊ ቁርኝት ያለውና ማራኪ ሃይማኖታዊ ሥርዓት የተጎናጸፈ መሆኑን ተናግረዋል። 

በዓሉ ሁሉም ሊጎበኘው የሚገባ ማራኪ ኃይማኖታዊ ሥርዓት የተጎናጸፈ መሆኑንም ገልጸዋል። 


 

ቬሮኒካ ሴድሮ የተባሉ ጎብኚም፤ ይህን ያህል ሕዝብ በአንድነት የሚያከብረው በዓል በሌሎች የዓለም ክፍሎች ያልተለመደና እጅግ ልዩ መሆኑን ጠቁመው፣ የማይረሳ ጊዜ እያሳለፉ እንደሚገኙ ገልጸዋል። 

ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት እነዚህን ድንቅ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ የመስህብ መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም