ቀጥታ፡

የከተራ በዓል የኢትዮጵያውያንን አብሮነት፣ ድንቅ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶችን ለዓለም የሚያሳይ ነው - ጎብኚዎች

አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2018(ኢዜአ)፦ የከተራ በዓል የኢትዮጵያውያንን አብሮነት፣ ድንቅ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶችን ለዓለም የሚያሳይ መሆኑን በጃንሜዳ የተገኙ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ገለጹ።

በአዲስ አበባ ከተማ ታቦታት በካህናት፣ በሰንበት ተማሪዎችና ምዕመናን ታጅበው በልዩ ሥነ-ሥርዓት ወደ ጥምቀተ ባሕሩ ጃንሜዳ ደርሰዋል።


 

በዓሉን ለመታደም የመጡ የውጭ ሀገራት ዜጎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የከተራ በዓል አከባበር የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክ፣ ሃይማኖታዊ ሥርዓትና ሕዝባዊ አንድነት በአንድ መድረክ የሚያሳይ ልዩ ትዕይንት ነው ብለዋል።

ከፈረንሳይ የመጡት ጎብኚ ማርክ ዳጉ በሰጡት አስተያየት፤ እንዲህ ያለ በርካታ ሕዝብ በአንድ ቦታ በፍቅር ተሰብስቦ ማየት እጅግ አስገራሚ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ምዕመናን ነጭ ባህላዊ አልባሳትን ለብሰው የሚያሳዩት ትዕይንት የኢትዮጵያን ውበትና ድምቀት ይበልጥ የሚያጎላ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ሌላኛዋ ፈረንሳዊ ጎብኚ ሶፊያን ገብርኤል በበኩላቸው፤ በዓሉ በሌሎች ሀገራት የማይታይ ድንቅ ክዋኔ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን እንግዶችን የሚቀበሉበት መንገድና የሚሰጡት ፍቅር በዓሉን ይበልጥ ማራኪ እንደሚያደርገው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

አዲስ አበባ ለቱሪስቶች ምቹና ውብ ከተማ መሆኗን የገለጹት ጎብኚዋ፤ ሌሎችም መጥተው እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።

በበዓሉ ላይ የታደሙ ጀርመናዊ ጎብኚ ራስ ሳቻ በበኩላቸው፤ በርካታ ሕዝብ በዓሉን በአንድነት ሲያከብር ማየቱ ታላቅ መንፈሳዊ ስሜት እንደሚፈጥር ገልጸዋል።


 

በዩኔስኮ የተመዘገበውን ታላቅ ዓለም አቀፍ ቅርስ ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ በዓሉ ለቱሪዝም ዕድገት ያለውን ሚና ከፍትኛ ነው ብለዋል።

ጎብኚዎቹ አክለውም፤ በዓሉ በዚህ መልክ ተጠብቆ ለትውልድ መሸጋገሩ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትልቅ ትምህርትና የመስህብ ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችን የመጎብኘት ፍላጎት እንዳላቸውም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም