ህዝበ ክርስቲያኑ የጥምቀት በዓልን ሲያከብር የአብሮነት እሴቱን ይበልጥ በማጠናከር ሊሆን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ህዝበ ክርስቲያኑ የጥምቀት በዓልን ሲያከብር የአብሮነት እሴቱን ይበልጥ በማጠናከር ሊሆን ይገባል
ጋምቤላ ፤ ጥር 10/2018 (ኢዜአ)፦ ህዝበ ክርስቲያኑ የጥምቀት በዓልን ሲያከብር የመደጋገፍና የአብሮነት እሴቱን ይበልጥ በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ የጋምቤላ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ አሶሳ፣ የቄለም ወለጋና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከትና የሲኖዶሱ አባል ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ገለጹ።
የጥምቀት ከተራ በዓል በጋምቤላ ከተማና አካባቢው በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በሊቃውንትና በሰንበት ተማሪዎች ያሬዳዊ ዝማሬ ታጅቦ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።
ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል በዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የጥምቀት በዓል የኢትዮጵያ ህዝቦች በአንድነትና በአብሮነት ደምቀው የሚታዩበት በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
ጥምቀት ሰማይና ምድርን የፈጠረው አምላክ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ እራሱን ዝቅ አድርጎ የተጠመቀበት የትህትና በዓል ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ምዕመኑ ከዚህ የሚወስደው ትምህርት ጥምቀት የትህትና፣ የፍቅርና የአንድነት በዓል መሆኑን ነው ብለዋል።
በመሆኑም ህዝበ ክርስቲያኑ የጥምቀት በዓልን ሲያከብር የመደጋገፍና የአብሮነት እሴቱን ይበልጥ በማጠናከር ያለው ለሌለው በማካፈል ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የጥምቀት በዓል ከኃይማኖታዊ ትውፊቱ ባለፈ ኢትዮጵያውያን በዓሉን ለመታደም ከተለያዩ የአለም ሀገራት ለሚመጡ ቱሪስቶች ፍቅርን፣ ትህትናንና አንድነትን የሚያሳዩበት በዓል መሆኑንም ገልጸዋል።
ምዕመኑ በዓሉን ሃይማኖታዊ ትውፊቱን በመጠበቅ በፍቅር፣ በትብብርና በአንድነት እንዲያከብርም ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል አሳስበዋል።