አርቲስት ነጻነት ወርቅነህ በሙያዊ ብቃትና ጥልቅ ዕውቀቱ የሚታወስ የጥበብ ሰው ነው - ኢዜአ አማርኛ
አርቲስት ነጻነት ወርቅነህ በሙያዊ ብቃትና ጥልቅ ዕውቀቱ የሚታወስ የጥበብ ሰው ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2018 (ኢዜአ)፦አርቲስት ነጻነት ወርቅነህ በሙያዊ ብቃትና ጥልቅ ዕውቀቱ የሚታወስ የጥበብ ሰው ነው ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ ገለፁ።
የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ሥርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ፣ የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ ከድር ጁሀር፣ የአርቲስቱ ቤተሰቦች፣ የሥራ ባልደረቦችና ወዳጅ ዘመዶቹ እንዲሁም በርካታ የአርቲስቱ አድናቂዎች ተገኝተዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ነብዩ ባዬ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ አርቲስት ነፃነት ወርቅነህ ሥራውን በሙያዊ ብቃትና በጥልቅ ዕውቀት ያከናውን እንደነበር ገልጸዋል።
አርቲስቱ ሙያዊ ስነ-ምግባር የተላበሰና ለኪነጥበቡ ዕድገት የበኩሉን ያበረከተ ታላቅ የጥበብ ሰው እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
በነፃነት ወርቅነህ ሥራዎች ላይ የተለያዩ የጥናት ሥራዎች ተካሂደው ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉና ለመማሪያነት እንዲያገለግሉ ይደረጋልም ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር በበኩላቸው፤ አርቲስት ነጻነት በሙያው ህዝብን እና ሀገርን ያገለገለ ታላቅ ባለሙያ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ለመላው ቤተሰቦቹ፣ አድናቂዎቹ፣ ለሙያ ባልደረቦቹ እና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም መጽናናትን ተመኝተዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጥበብ ባለሙያዎች በበኩላቸው፤ አርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስራውን በጥልቅ ፍቅርና በሙያዊ ስነ-ምግባር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
አርቲስት ሰለሞን ታሼ ፤ ነጻነት ወርቅነህ ሥራውን በከፍተኛ ስነ-ምግባርና ዝግጅት የሚያከናውን ድንቅ የጥበብ ሰው እንደነበር ጠቅሷል፡፡
ለሙያ ባልደረቦቹም ትልቅ አክብሮትና ፍቅር የነበረው ታላቅ የጥበብ ሰው እንደነበርም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
በፊልም እና በቴአትር ተዋናይነት፣ በቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢነት እንዲሁም በሌሎች የጥበብ ሥራዎቹ ስመጥርና ተወዳጅ የሆነው አርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ባለትዳር እና የሶስት ልጆች አባት ነበር።