በክልሉ አደረጃጀቶችን በማጠናከር የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ አደረጃጀቶችን በማጠናከር የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል
ባህርዳር ፤ ጥር 10/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል አደረጃጀቶችን በማጠናከር ልማትንና ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱን በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት አስታወቀ።
"ጠንካራ አደረጃጀት ለጠንካራ ፓርቲ" በሚል መሪ ሃሳብ በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማውን እያካሄደ ነው።
በፅህፈት ቤቱ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍስሃ ደሳለኝ በመድረኩ ላይ እንደገለፁት፤ አደረጃጀቶችን በማጠናከር ሁለንተናዊ ልማትንና ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል።
በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት የልማት አቅሞችን አቀናጅቶ በመስራት የታቀዱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን በውጤታማነት ማከናወን መቻሉን አመልክተዋል።
አደረጃጀቶች የፓርቲና የመንግስት ተልዕኮን መፈፀም ዋነኛ ግባቸው ነው ያሉት አቶ ፍስሃ፤ የክልሉን ሁለንተናዊ ልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለማቀላጠፍ ግንባር ቀደም ሚናቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአደረጃጀቶች የጠራ ሃሳብና ግልጽ የትግበራ አቅጣጫ በመያዝ የልማት ስራዎችን ማከናወን የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መሰጠታቸውንም አስረድተዋል።
በዚህም የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለማሳካት አመራሩ ግንባር ቀደም ሆኖ መሰለፉን ተናግረዋል።
ተግባሩም በቀጣይ የሀገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥና ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለመገንባት ተደማሪ አቅም መፍጠሩን አስረድተዋል።
በመድረኩ ከክልል ጀምሮ በተዋረድ የሚገኙ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙም ታውቋል።