አስተዳደሩ የዜጎችን ኑሮ የሚያሻሽሉ ሰው ተኮር ተግባራትን አጠናክሮ ይቀጥላል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
አስተዳደሩ የዜጎችን ኑሮ የሚያሻሽሉ ሰው ተኮር ተግባራትን አጠናክሮ ይቀጥላል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2018 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የሚያከናውናቸውን የሰው ተኮር ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 መካኒሳ አቦ ማዞሪያ አካባቢ ቀደም ሲል በጉሊት ንግድ ላይ ተሰማርተው ለቆዩ እናቶች የተገነቡ ዘመናዊ የንግድ ሱቆችን አስረክበዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ እነዚህ እናቶች ቀደም ሲል ፀሀይ፣ አቧራና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው ሥራቸውን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በማከናወን ቤተሰቦቻቸውን ሲያስተዳድሩ እንደቆዩ አስታውሰዋል።
የኮሪደር ልማት ከመሰራቱ በፊት ጉሊት ቦታ የሆነውን በመቀየር ዘመናዊ የመሸጫ ቦታ መሰራቱን ጠቅሰው፤ በከተማዋ እየተካሄደ ያለው ልማት የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የዜጎችን የሥራ አካባቢ ምቹና ዘመናዊ ማድረጉን ገልጸዋል።
በከተማዋ የሚከናወኑ ማንኛውም የልማት ስራዎች ሰው ተኮርና የነዋሪውን ሕይወት የሚቀይሩ መሆናቸውን ከንቲባዋ ተናግረዋል።
ዛሬ የመስሪያ ቦታ የተረከቡ እናቶችም ለሽያጭ የሚያቀርቡትን ምርት በቀላሉ እንዲያገኙ ከላፍቶ ገበያ ማዕከል ጋር የገበያ ትስስር እንደተፈጠረላቸው አስታውቀዋል።
እናቶች በምቹ ሁኔታ እንዲነግዱና የአካባቢው ማኅበረሰብም ምርቶችን ከእነዚሁ እናቶች በመግዛት እንዲያበረታታቸው ጥሪ አቅርበዋል።