የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ - ኢዜአ አማርኛ
የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ
አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2018 (ኢዜአ)፦ የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ሥርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ የአርቲስቱ ቤተሰቦች፣ የሥራ ባልደረቦችና ወዳጅ ዘመዶቹ እንዲሁም በርካታ የአርቲስቱ አድናቂዎች ተገኝተዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ነብዩ ባዬ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ አርቲስት ነፃነት ወርቅነህ ሥራውን በሙያዊ ብቃትና በጥልቅ ዕውቀት ያከናውን እንደነበር ገልጸዋል።
አርቲስቱ ለሙያው ዲሲፕሊንና ለጥበብ ጥራት ትልቅ ትኩረት የሚሰጥ የጥበብ ሰው እንደነበርም አክለዋል።
በነፃነት ወርቅነህ ሥራዎች ላይ ጥናት ተደርጎ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍና እንደ መማሪያ እንዲያገለግል እንደሚደረግም ተናግረዋል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፤ አርቲስት ነጻነት በሙያው ህዝብን እና ሀገርን ያገለገለ ታላቅ ባለሙያ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ለመላው ቤተሰቦቹ፣ አድናቂዎቹ ፣ ለሙያ ባልደረቦቹ እና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም መጽናናትን ተመኝተዋል:፡
በፊልም እና በቴአትር ተዋናይነት፣ በቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢነት እንዲሁም በሌሎች የጥበብ ሥራዎቹ ስመጥርና ተወዳጅ የሆነው አርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ጥር 8 ቀን 2018 ዓ.ም በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ይታወሳል።