ቀጥታ፡

አስቶንቪላ ከኤቨርተን ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2018(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ አስቶንቪላ ከኤቨርተን በቪላ ፓርክ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

አስቶንቪላ በ43 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። ኤቨርተን በ29 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሁለቱ ክለቦች በሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለ81ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 80 ጨዋታዎች አስቶንቪላ 40 ጊዜ ድል ሲቀናው ኤቨርተን በ22ቱ ድል ቀንቶታል። በቀሪ 18 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

በ80 ጨዋታዎች አስቶንቪላ 102 ግቦችን ሲያስቆጥር ኤቨርተን 79 ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፏል። 


 

ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች በነበራቸው ግንኙነት አስቶንቪላ ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

ኤቨርተን ለመጨረሻ ጊዜ አስቶንቪላን በሊጉ ያሸነፈው እ.አ.አ ማርች 1 2016 ሲሆን በወቅቱ የ3 ለ 1 ድል ተቀዳጅቷል።

ቡድኖቹ በዘንድሮው የውድድር ዓመት በአራተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ባደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

አስቶንቪላ ካሸነፈ ከሊጉ መሪ አርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ዝቅ ያደርጋል። 

ኤቨርተን ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

ቶኒ ሃሪንግተን ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

በሌላኛው መርሃ ግብር ዎልቭስ ከኒውካስትል ዩናይትድ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም