ቀጥታ፡

የአፍሪካ ዋንጫን ማን ያነሳል?  ሴኔጋል ወይስ አዘጋጇ ሞሮኮ?

አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2018 (ኢዜአ)፦  በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ መርሃ ግብር ሴኔጋል እና ሞሮኮ ዛሬ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

አሸናፊው ሀገር ከዋንጫው በተጨማሪ 10 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወደ ካዝናው ያስገባል። 

የብሄራዊ ቡድኖቹ ጨዋታ ምሽት አራት ላይ በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም ይካሄዳል። 

ጨዋታው የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ትኩረት ስቧል።

በግማሽ ፍጻሜው ሴኔጋል ግብጽን፣ ሞሮኮ ናይጄሪያን በማሸነፍ ለዋንጫው ፍልሚያ ቀርበዋል።

የፍጻሜ ተፋላሚ ሀገራቱ በዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ ሽንፈት አላስተናገዱም።


 

ሴኔጋል በውድድሩ ላይ እስከ አሁን ስድስት ጨዋታዎችን አድርጋ አምስቱን ስታሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ተለያይታለች። በጨዋታዎቹ ላይ 12 ግቦችን ስታስቆጥር ሁለት ግቦችን አስተናግዳለች።

አዘጋጇ ሞሮኮ ካደረገቻቸው ስድስት ጨዋታዎች መካከል አራቱን ስታሸንፍ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥታለች።

በጨዋታዎቹ ላይ ዘጠኝ ግቦችን ከመረብ ላይ ስታሳርፍ የተቆጠረባት አንድ ጎል ብቻ ነው። ሞሮኮ በውድድሩ ላይ ዝቅተኛ የግብ መጠን የተቆጠረባት ሀገር ናት።

ሴኔጋል እና ሞሮኮ በአፍሪካ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም በውድድር እና በወዳጅነት ጨዋታዎች በአጠቃላይ 33 ጊዜ ተገናኝተዋል። ሞሮኮ 18 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች። ሴኔጋል በሰባቱ ስታሸንፍ በቀሪ ስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

ሞሮኮ በጨዋታዎቹ ላይ 41 ግቦችን ስታስቆጥር፣ ሴኔጋል 17 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፋለች። 

ሁለቱ ሀገራት ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ ኦገስት 2025 በኬንያ፣ ዩጋንዳ እና ታንዛንያ ጣምራ አዘጋጅነት በተካሄደው ስምንተኛው የአፍሪካ ሀገራት ሻምፒዮና (ቻን)ላይ ነበር።

በግማሽ ፍጻሜው ተገናኝተው ሞሮኮ ሴኔጋልን በመለያ ምት 4 ለ 2 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፋለች። ሞሮኮ በፍጻሜው ማዳጋስካርን በመርታት ዋንጫውን አንስታለች።

ሀገራቱን በዘንድሮው ውድድር ከሚያመሳስላቸው ጉዳዮች አንዱ ከጨዋታ ጨዋታ ይበልጥ ጥንካሬያቸውን እና አቅማቸውን እያሳደጉ መምጣታቸው ነው።

ሴኔጋል ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት፣ ማጥቃት እና መከላከል ላይ ተመጣጣኝ ሚዛን በመስራት የሚጫወተው የአማካይ ክፍል፣ የማጥቃት አቅም እና በድንቅ ብቃት ላይ የሚገኘው ግብ ጠባቂ ኤድዋርድ ሜንዲ የጥንካሬዎቿ ማሳያ ናቸው።

በተወሰኑ ተጫዋቾች ላይ ጥገኛ መሆን እና ለፈጣን መልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ተጋላጭ መሆን እንደ ድክመት ይነሳል።


 

አዘጋጇ ሞሮኮ ቅርጹን የጠበቀ እና በቀላሉ ሰብሮ መግባት የማይቻል የተከላካይ ክፍል ገንብታለች። የቀኝ እና ግራ መስመር ተመላላሽ ተጫዋቾች የማጥቃት ብቃት፣ በክህሎት የተሞላው የአማካይ ክፍል እና ከተለያዩ አማራጮች ግብ ማስቆጠር መቻሏ እንደ ጥንካሬ የሚነሳ ነው።

በጣም ጥንቃቄ የታከለበት የሞሮኮ የኳስ ቅብብል በጣም ተጭነው እና ፍሰትን ለማበላሸት በሚጫወቱ የተጋጣሚ ቡድኖች ለአደጋ የተጋለጠ ሲሆን ይህም የማጥቃት አቅምን ሲቀንስ ታይቷል። 

ሞሮኮ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ በጥልቀት የሚጫወቱ ቡድኖችን አስከፍታ ለመጫወት ስትቸገር ለመመልከት ተችሏል።

በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር እና ሶስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ያቀበለው ሳዲዮ ማኔ የሴኔጋል ቁልፍ ተጫዋች ነው።

አምስት ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ የውድድሩ ክስተት የሆነው የሞሮኮው ብራሂም ዲያዝ በጨዋታው ላይ ልዩነት ይፈጥራሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተጫዋቾች መካከል ይገኝበታል።

ጨዋታው በታክቲክ የታጠረ እና ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል።


 

ሴኔጋል እ.አ.አ በ2022 በካሜሮን አስተናጋጅነት የተካሄደውን 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ያነሳች ሲሆን ውድድሩን ለሁለተኛ ጊዜ ለማሸነፍ ትጫወታለች።

ተጋጣሚዋ ሞሮኮ ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1976 ባዘጋጀችው 10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ብቸኛ አህጉራዊ ድሏን ማሳካት ችላለች።  ከ50 ዓመታት ራሷ ያዘጋጀችውን ዋንጫ ለመውሰድ ትፋለማለች።

አሸናፊው ሀገር ከዋንጫው በተጨማሪ የ10 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ያገኛል። ይህም ከ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የ43 በመቶ ብልጫ እንዳለው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።

ሁለተኛ የሚወጣው ሀገር የአራት ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ያገኛል። አጠቃላይ ለተሳታፊ ሀገራት የ32 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ይበረከታል።

ከታህሳስ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም