የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በዓሉን በባህል አልባሳት ደምቀው ለማክበር ተዘጋጅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በዓሉን በባህል አልባሳት ደምቀው ለማክበር ተዘጋጅተዋል
ጎንደር ፤ ጥር 10/2018 (ኢዜአ)፦ በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓልን በባህል አልባሳት ደምቀው ለማክበር መዘጋጀታቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
"ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ" ይላሉ አበው የጥምቀትን ድምቀት ለመግለጽ።
ጥምቀት ሰዎች አምረውና ተውበው የሚወጡበት የአደባባይ በአል ነው።
በአሉ ከመንፈሳዊ አስተምህሮው በሻገር ማህበራዊና ባህላዊ ትዕይንቶች የሚስተዋሉበትም ነው።
በገጠሩ አርሶ አደሩ ሰብሉን ሰብስቦ አንጻራዊ እረፍት የሚያገኝበትና ወጣቶች የትዳር አጋራቸውን የሚያጩበት በመሆኑም አምሮ መውጣት የተለመደ ነው።
ይህንን ተከትሎም ሰዎች ከቻሉ አዲስ ገዝተው አሊያም ያላቸውን አጥበው በአሉን በመታደም ደምቀው መታየት የጥምቀት መገለጫ ነው።
ይህ ባህላዊና መንፈሳዊ ክዋኔ በተለየ መንገድ በድምቀት በሚታይባት የጎንደር ከተማ ኢዜአ የባህል አልባሳት ገበያውን ቃኝቷል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወጣት ትእግስት አንተነህ፤ በጥምቀት በአል አዲስ የባህል ቀሚስ መግዛቷንና ዋጋውም ተመጣጣኝ መሆኑን ገልጻለች፡፡
የባህል አልባሳት በጥራትና በዓይነት ተዘጋጅተው ለገበያ በመቅረባቸው የምርጫውን ገዝቶ በአሉን በድምቅት ለማክበር መዘጋጀቱን የገለጸው ደግሞ ወጣት ቢኒያም አሰፋ ነው።
የባህል አልባሳት የማንነታችን መገለጫ፤ ዘመን ተሻጋሪ ውርሶቻችን ናቸው ያለው ወጣት ቢኒያም፤ በበአሉ ደምቆ ለመታየት ተስማሚ የሆነ የባህል ልብስ መግዛት እንደቻለ ገልጿል፡፡
ከጊዜው ጋር የዘመኑና ትውልዱ የሚፈልጋቸው ባህላዊ አልባሳት በተለያዩ ዲዛይኖች ተዘጋጅተው ለገበያ እየቀረቡ ናቸው ያሉት ደግሞ በባህል አልባሳት ስፌት የሚተዳደሩት አቶ ሀምዛ እሸቱ ናቸው፡፡
ለወንድም ሆነ ለሴት ተመራጭና ምቹ የሆኑ የባህል አልባሳትን በልዩ ዲዛይን ሰፍተው በማዘጋጀት ለበአል ገበያው እያቀረቡ መሆኑን ጠቁመው፤ ገበያውም የደራ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ቅዳሜ ገበያ ተብሎ በሚጠራው የከተማው የባህል አልባሳት ገበያ የጎንደር ቀሚስ ከአምስት እስከ ሰባት ሺህ ብር እየተሸጠ ነው፡፡
የወንድ ጃኖ አልባሳት ደግሞ ከአምስት ሺህ እስከ ስድስት ሺህ ብር ለገበያ የቀረበ ሲሆን በጥልፍ ዲዛይን የተዘጋጀ ከላይ የሚለበስ የባህል ልብስ ደግሞ ከሶስት ሺህ እስከ አራት ሺህ ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡