የገበታ ለትውልድ ሥራ የመጀመሪያው መዳረሻ የሆነው ደንቢ ኢኮ ሎጅ በይፋ ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የገበታ ለትውልድ ሥራ የመጀመሪያው መዳረሻ የሆነው ደንቢ ኢኮ ሎጅ በይፋ ተመረቀ
አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2018 (ኢዜአ)፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የገበታ ለትውልድ ሥራ የመጀመሪያው መዳረሻ የሆነው እና በ36.7 ሔክታር የጥብቅ ደን እና የተፈጥሮ ኃብት ስጦታ የተዘረጋው ደንቢ ኢኮ ሎጅ በይፋ ተመርቋል።
ኢኮ ሎጁ የሀገራችን የቱሪዝም ዘርፍ ባለፉት ሰባት ዓመታት ዘላቂነትን፣ የቅርስ ሀብትን እና ለዘመናት የሚዘልቅ ዓለም አቀፍ ደረጃን የመጠበቅ ዕድል መፍጠርን በማዋሃድ ምን ያህል እንደተለወጠ ማሳያ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ገልጿል።
የገበታ ለትውልድ ሥራ ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቁ መዳረሻዎችን በማልማት የሀገራችንን እምቅ አቅም ለማውጣት የሚደረገው የሰፊው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ስትራቴጂ አካል ነውም ብሏል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው ይኽ ሥራ በስኬት ከተተገበሩት የገበታ ለሸገር እና ገበታ ለሀገር መርሐ-ግብሮች የቀጠለ እና ሥራዎቹን ወደአዳዲስ አካባቢዎች የወሰደ ሲሆን የተፈጥሮ ውበትን፣ የባሕል ቅርስን እና ዘላቂ ልምድን በማቀናጀት የተከናወነም መሆኑ ተመላክቷል።
እነዚህ ሥራዎች የከተማ እና ተፈጥሯዊ መዳረሻዎችን ወደ ሳቢ የቱሪዝም ማዕከልነት የለወጡ መሆናቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።