ቀጥታ፡

ተፈጥሯዊ ፀጋዎችን ተጠቅመን የዜጎቻችንን ኑሮ መቀየር ከቻልን የተሟላ ብልጽግና እናመጣለን- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፡- በሀገር ደረጃ በየአካባቢው ያሉ ተፈጥሯዊ ፀጋዎችን ለይተን በመጠቀም የዜጎቻችንን ኑሮ መቀየር ከቻልን የተሟላ ብልጽግና እናመጣለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጉራፈርዳ ወረዳ የገጠር ኮሪደርን ጎብኝተዋል።

ከጉብኝታቸው በኋላም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በሰጡት ገለጻ፤ ጉራፈርዳ ወረዳ በለምነቱ፣ በሚያመርተው ቡና፣ በልዩ ልዩ የግብርና ምርቶች እንደሚታወቅ እና ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ዜጎች በጋራ የሚኖሩበት መሆኑን አንስተዋል።

በከተማ የጀመርነውን የኮሪደር ልማት ሥራ ወደ ገጠር እናምጣ ብለን እየሠራን ባለው ሥራ፤ በሁሉም ክልሎች አዳዲስ የተሻገሩ የገጠር መንደሮች እየተገነቡ ይገኛሉ ሲሉም አስታውቀዋል።


 

በጉራፈርዳ ወረዳ በተሠራው የገጠር ኮሪደርም የጓሮ አትክልት፣ ዶሮ፣ የወተት ላሞችና ማርን ጨምሮ የሌማት ትሩፋት መመልከታቸውን ጠቅሰዋል።

በእያንዳንዱ ጓሮ ይህ ካለ በአካባቢው ካሉ የእርሻ ውጤቶች ጋር ተደምረው በቂ ምግብ የሚያገኙበትን ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።

ስለዚህ በሀገር ደረጃ እንደየ አካባቢው ተፈጥሯዊ ፀጋዎችን ለይተን በመጠቀም የዜጎቻችንን ኑሮ መቀየር ከቻልን የተሟላ ብልጽግና ማምጣት እንችላለን ሲሉ አስገንዝበዋል።

በወረዳው የተገነባው የገጠር ኮሪደር ልማት መዋዕለ-ሕጻናት ማካተቱ ከሌላው እንደሚለየውም ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ ብልጽግናን እናረጋግጥ ሲባል በቁጥር የሚታይ ዕድገት ብቻ ሳይሆን፤ በከተማም በገጠርም እያንዳንዱን ዜጋ መንካት አለበት ማለት ነው ብለዋል።


 

ክልሉ ያለውን ጸጋ በመጠቀም የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል መሥራት እንደሚጠበቅበትም አመላክተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እስካሁን የተሠሩትና እየተሠሩ ያሉ የገጠር ኮሪደሮች ሞዴል መሆናቸውን ገልጸው፤ ክልሎች፣ ባለሃብቶች፣ ዞኖች እንዲሁም ነዋሪው በራሱ ወጪው ቀላል መሆኑን በመረዳት ማስፋትና ማስቀጠል እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።

በስንዴ፣ በቡና፣ በሌማት ትሩፋት ያገኘነው ውጤት የዜጎችን ኑሮ መቀየር አለበት በሚል የጀመርነው የገጠር ኮሪደር ሥራ ፍሬ እያፈራ ነው ብለዋል።

ስለዚህ በቀጣይ በይበልጥ እንዲስፋፋ አሳስበው፤ ተባብረን በመሥራት የዜጎቻችንን ኑሮ እንድንቀይር አደራ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም