ቀጥታ፡

የግብር ከፋዩ ለሀገር ዕድገት ያለው ቁርጠኝነት ማደግ ስኬታማ ለውጥ እንዲመዘገብ አግዟል- ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሤ

አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፦ ግብር ከፋዩ የሚከፍለው ግብር ለሀገር ዕድገት እንደሚውል ያለው ግንዛቤና ታክስ የመክፈል ቁርጠኝነት ማደግ ስኬታማ የታክስ አሰባሰብ እንዲኖር ማገዙን የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሤ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ''የፋይናንስ እመርታ በኢትዮጵያ'' በሚል ሐሳብ በተካሄደ ኮንፈረንስ ላይ የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሤ ገለጻ አድርገዋል።

ሚኒስትሯ የታክስ አሥተዳደር ሪፎርም ለኢኮኖሚ ዕድገት እና ቀጣይነት በሚል ርዕሰ ጉዳይ ባቀረቡት ገለጻ፤ የታክስ አሥተዳደር አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻልና የማስፈጸም ዐቅምን ማጠናከር፣ ዘመናዊ የታክስ አሥተዳደር ሥርዓት መገንባት፣የታክስ ሕግ ተገዥነትን ማረጋገጥ እና ዘላቂ የገቢ ዕድገት ማረጋገጥ በሚሉት ዐበይት ጉዳዮች ላይ ሪፎርሙ መከናወኑን አንስተዋል።

ከላይ በተገለጹት ጉዳዮች ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣትም በሪፎርሙ ወቅት የፖሊሲ እና የሕግ ማሻሻዎች መደረጋቸውን ጠቁመው፥ እነዚህን ለመፈጸምም የአሠራር ማሻሻያዎች ተደርገዋል ብለዋል።

ቅርንጫፎች ማስፋፋትን ጨምሮ ከፌደራል እስከ ክልል ባሉ ባለድርሻ አካላት ዘንድ ስኬታማ ተግባራት ለማስመዝገብ እንዲቻል የዐቅም ግንባታ ሥራዎች መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል።

እንደ ሀገር የተጣጣመ የታክስ አሥተዳደር ሥርዓት እንዲኖር ጥረቶች መደረጋቸውንም አመላክተዋል።

የዲጂታል ሥርዓቶችን በመዘርጋት ለግብር ከፋዮች ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር አንጻር ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተው፤ ለአብነትም መሠረታዊ የሚባሉ የዲጂታል ፕላት ፎርሞች መዘርጋታቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም መሠረት ግብር ከፋዩ በየቢሮው መሄድ ሳይጠበቅበት ኢ-ፋይል እና ኢ-ፔይ የሚያደርግበትን ሥርዓት ዘርግተናል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል በኢንሳ አማካኝነት ለምቶ በቅርቡ ወደ ሥራ እያስገባነው ባለው የኤሌክትሮኒክ ኢንቮይሲንግ ሲስተም በትራንዛክሽን ደረጃ ወደ 291 ቢሊየን ብር ግብይት ተካሂዶበታል ብለዋል።

ይህም ከሐሰተኛ ደረሠኝ፣ ከውሳኔ አሰጣጥ፣ ከመረጃ አጠቃቀም እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን የሚቀርፍ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ከጉምሩክ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘም አሁን ላይ የወጪና ገቢ ንግድን ከማሳለጥ አንጻር በአንድ መስኮት አገልግሎት ከ80 በላይ ተቋማት በአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በሌላ በኩል ኢኮኖሚውን በዘላቂነት የሚደግፍ ወደ ሉዓላዊነት የሚወስደን ገቢ በሀገር ውስጥ መመንጨት አለበት በሚል የተከናወነው ሥራ የሪፎርሙን ስኬት አሳይቷል ነው ያሉት።

በዚህም መሠረት በ2011 የበጀት ዓመት የፌደራል መንግሥት 198 ቢሊየን ብር ታክስ መሰብሰቡን አውስተው፤ በ2017 ደግሞ 900 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።

በተያዘው ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ደግሞ 907 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ገልጸው፤ ይህ አሃዝ ከዕቅዳችን አንጻር ወደ 68 ቢሊየን ብር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻርም የ258 ቢሊየን ብር ብልጫ ማሳየቱን አንስተዋል።

ይህም በየደረጃው ያሉ አካላት ድጋፍ፣ የግብር ከፋዮች ሀገርን ለመለወጥ ያለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ያላቸው ቁርጠኝነት ውጤት መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።

ከክልሎች አኳያም በ2011 የታክስ ገቢ 79 ቢሊየን ብር ብቻ እንደነበር አውስተው፤ በ2017 ደግሞ 543 ቢሊየን ብር መሰብሰባቸውን ተናግረዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመት እንደ ሀገር ከ2 ነጥብ 1 ትሪሊየን ብር በላይ ታክስ ለመሰብሰብ መታቀዱን እና ባለፉት ስድስት ወራት 1 ነጥብ 17 ትሪሊየን ብር ታክስ መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም