ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት በዲጂታል አማራጭ በመላ ሀገሪቱ ተደራሽነቱን እያሰፋ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት በዲጂታል አማራጭ በመላ ሀገሪቱ ተደራሽነቱን እያሰፋ መሆኑን አገልግሎቱ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ  ሙሉጌታ ታደሰ ገለጹ።

በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የተደረገው 60 ሚሊየን ብር ተሸላሚ የሚያደርገው ዲጂታል ሎተሪ ዕጣ በኢትዮጵያ  ሎተሪ አገልግሎት እድል አዳራሸ ወጥቷል።

በእጣ አወጣጥ ስነ ሰርዓቱ ላይ  የመንግስት ተቋማት ሀላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላትና ታዛቢዎች ተገኝተዋል።


 

የ60 ሚሊየን ብር ዕጣው 6361547፤ 20 ሚሊየን ብር ተሸላሚ የሚያደርገው እጣ 5681025 እንዲሁም 10 ሚሊየን ብር ተሸላሚ የሚያደርገው ዕጣ 7699884 እንዲሁም ማስተዛዘኛ ቁጥር 4 ሆኖ ወጥቷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ  የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ ታደሰ እንደተናገሩት፤ የ60 ሚሊየን ብር ዲጂታል ሎተሪ በሽልማት ከፍተኛው መሆኑና ለመጀመሪያ ጊዜ በዲጂታል ብቻ መቅረቡ ልዩ  ያደርገዋል። 

ደንበኞች በየትኛውም ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ በፖዝ ማሽን፣ በድረ ገጽና በተለያዩ የዲጂታል አማራጮች መሳተፍ መቻላቸውን ገልጸዋል።

ይህም የሎተሪን ስራ ወጪ ቆጣቢ ፈጣንና ተደራሽ ማድረጉን ገልጸው፤ ደንበኞች በፍጥነትና በቀላሉ እንዲሳተፉ አስችሏል ብለዋል።


 

በኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ቴድሮስ ነዋይ በበኩላቸው፤ ዲጂታል ሎተሪ ሙሉ ለመሉ በዲጂታል መከናወኑ አገልግሎቱን ቀልጣፋ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው፤  አሰራሩም ለደንበኞች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንና ተሸላሚዎችን በቀላሉ ለማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።

በታምኮል ሶፍትዌር ሶልዩሽንስ የሳይበር ደህነነት ክፍል ሀላፊ አንማው ቃሬ የሎተሪ አገልግሎትን ለማዘመንና ዲጂታላይዝ ለማድረግ  በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ይህም የሎተሪ አገልግሎትን ከዝግጅት ጀምሮ እስከ ሽልማት ማውጣትና ደንበኞችን መለየት ደረጃ ድረስ በዲጂታል ለማከናወን አስችሏል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም