የዋግ ልማት ማህበር የልማት ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያከናውነውን ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የዋግ ልማት ማህበር የልማት ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያከናውነውን ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል
ሰቆጣ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፡-የዋግ ልማት ማህበር በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የልማት ክፍተቶችን ለመሙላት እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የልማት ማህበሩ አስታወቀ።
የዋግ ልማት ማህበር 13ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በሰቆጣ ከተማ እያካሄደ ነው።
የልማት ማህበሩ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ መልሰው ተፈራ (ዶ/ር) በጉባኤው እንዳሉት ልማት ማህበሩ ባለፉት ዓመታት በብሔረሰብ አስተዳደሩ መንግስት ከሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን አከናውኗል።
ደረጃቸውን ያልጠበቁ መማሪያ ክፍሎችን በአዲስ መልክ አሻሽሎ ከመስራት ባለፈ የጤና ተቋም ተደራሽ ባልሆኑባቸው አካባቢዎች የጤና ተቋማት ግንባታ ማከናወኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ልማት ማህበሩ በብሔረሰብ አስተዳደሩ የልማት ክፍተቶችን ለመሙላት ሲያከናውን የቆያቸውን ተግባራት በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል መልሰው (ዶ/ር) ገልፀዋል።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪና የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሹመት ጥላሁን እንዳሉት ልማት ማህበሩ በአስተዳደሩ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ የሚስተዋሉትን የልማት ክፍተቶች ለመሙላት የተለያዩ የልማት ስራዎችን ማከናወኑን ጠቁመዋል።
የልማት ማህበሩ ህብረተሰቡን በማስተባበር በተለይ በትምህርት፣ በጤና እና በሰብዓዊ ድጋፎች ያከናወናቸው ተግባራት የህብረተሰቡን ችግር እያቃለሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ የልማት ማህበሩ እያደረገ ያለው አስተዋጾን ማጠናከር በራስ አቅም የመረዳዳት ባህልን ለማሳደግ ትልቅ አቅም ይሆናል ሲሉም አቶ ሹመት ገልፀዋል።
ልማት ማህበሩ የዋግ ህዝብ ሃብት በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ማህበሩን በተለያየ መንገድ በማገዝ የልማት ክፍተቶችን ለመድፈን የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
ጉባኤው የልማት ማህበሩ ያለፉት ሦስት ዓመታት ተግባራት አፈፃፀምና የኦዲት ሪፖርትን ከመገምገም ባለፈ የልማት ማህበሩ መመሪያ እና የቦርድ አባላት ምርጫን በተመለከተ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን ገምግሞ እንደሚያጸድቅ ተመላክቷል።