ቀጥታ፡

የብዝሀ ዘርፍ ኢኮኖሚ ትግበራው በሚፈጥረው የሥራ ዕድል ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል

ሆሳዕና፤ ጥር 9/2018(ኢዜአ)፡-የብዝሀ ዘርፍ ኢኮኖሚ ትግበራው ለሀገር ውስጥ የሥራ ስምሪት በፈጠረው የሥራ ዕድል ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ እንደሚጠናከር የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ለኢዜአ እንደገለጹት የብዝሀ ዘርፍ ኢኮኖሚ ትግበራው ለሀገር ውስጥ የሥራ ስምሪት የፈጠረውን ዕድል ለዜጎች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ግብ ተጥሎ ባለፉት 6 ወራት በግብርና ፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎችን በብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ትግበራው በተፈጠረ የሥራ እድል በሀገር ውስጥ የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ ለማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

ቀሪው የውጪ ሀገር የሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂን በመጠቀም በርቀት የተፈጠረ የሥራ ዕድል መሆኑንም አስረድተዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ በሥራ ዕድል ፈጠራ ከልየታ እስከ ሥራ ስምሪት ድረስ ያለው ተግባር የተከናወነው የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ አጠቃቀምን መሰረት ባደረገ መልኩ ነው፡፡

ለዜጎች የተፈጠረው የሥራ ዕድል ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በመሆኑ በሁሉም ክልሎች በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ መምጣቱንም ጠቅሰዋል።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል ለማህበረሰቡ ተጠቃሚነት መረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም