ቀጥታ፡

‎‎‎‎በክልሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የስፖርት ማዘውተሪያ ልማት ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ነው

ዲላ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ) ፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ‎ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የስፖርት ማዘውተሪያ ልማት ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የታዳጊዎች ምዘናና የባህል ስፖርት ውድድር ፌስቲቫል ዛሬ በዲላ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።


 

በመርሀ ግብሩ መክፈቻ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) እንዳሉት በክልሉ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎች ወደ ስፖርት መምጣት እንዲችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

ከነዚህ ተግባራት መካከል ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚያስችሉ የስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታ ስራ ዋናው መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ከከተሞች ኮሪደር ልማት ጋር በማስተሳሰር የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራ ልማት እየተከናወነ መሆኑን አንስተው ይህም ተተኪ ስፖርተኞች ለማፍራት ድርሻው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ዛሬ የተጀመረው ታዳጊዎች ምዘናና የባህል ስፖርት ውድድር ተሳታፊዎችም ስፖርታዊ ጨዋነትን በመላበስ ወንድማማችነትን እና እህትማማችነትን ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ውድድሩ የታዳጊ ወጣቶችን አቅም በማጎልበት ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ዓላማ ያደረገ ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ባህልና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኦላዶ ኦሎ ናቸው።

ፌስቲቫሉ ከውድድርና ምዘና ባለፈ የክልሉ ህብረ ብሔራዊነትና ቱባ ባህሎች በአደባባይ የሚንጸባረቅበትና አንድነት የሚጎላበት መድረክ ነው ብለዋል።

በውድድሩ ላይ በክልሉ ከሚገኙ 12 የዞንና ሶስት ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ታዳጊ ስፖርተኞች የሚሳተፉ ሲሆን በተለይ በእግር ኳስ ረገድ ክልሉን ወክለው በሃገር ደረጃ የሚሳተፉ 33 ታዳጊዎች ምልመላ እንደሚከናወን አንስተዋል።

ውድድሩ ከ11 በላይ ባህላዊና ዘመናዊ ስፖርቶችን በሁለቱም ጾታዎች ያቀፈ መሆኑን ጠቅሰው ከ1 ሺህ 600 በላይ የስፖርት ልዑካን እንደሚሳተፉም ተናግረዋል።

የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ  መስፍን ደምሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፌስቲቨሉ በከተማው መካሄዱ የስፖርት እንቅስቃሴን ከማነቃቃት ባለፈ የከተማዋን ገጽታ ለመገንባት ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል።

በተለይ በከተማው የሚገኙ ታዳጊ ስፖርተኞች በውድድሩ ከመሳተፍ ባለፈ ልምድ በመቅሰም ተወዳዳሪነታቸውን የሚያጠናክሩበት መልካም አጋጠሚ መሆኑን አንስተዋል።

በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የክልል፣ የዞንና የከተማ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የሁሉም መዋቅሮች የስፖርት ልዑካንና የስፖርቱ ቤተሰብ ተሳተፊ ሆነዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም