ቀጥታ፡

የክልሉን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የወጣቱን እውቀት፣ ጉልበትና ፈጠራ ለመጠቀም ትኩረት ተደርጓል

ባህርዳር ጥር 9/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል  እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የወጣቱን እውቀት፣ ጉልበትና ፈጠራ ለመጠቀም ትኩረት መደረጉን የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ። 

ቢሮው በክልሉ የ25 ዓመት የአሻጋሪ እቅድ ላይ በክልሉ የሚገኙ ወጣት የመንግስት ሰራተኞችን ያሳተፈ መድረክ ዛሬ በባህርዳር ከተማ አካሂዷል።


 

በቢሮው የወጣቶች ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ዘላለም አረጋ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት የክልሉን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የወጣቱን እውቀት፣ ጉልበትና ፈጠራ ለመጠቀም የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።

አሁን የሚስተዋሉ ችግሮችን በማስወገድ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ልማትን ለማፋጠን በሁሉም መልኩ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው የክልሉ ወጣት የ25 ዓመት የአሻጋሪ የልማት እቅድ ላይ ግንዛቤ በመያዝ፣ ለአተገባበሩ አቅሙን መጠቀም እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በተለይም የክልሉን ህዝብ ከድህነት ለማላቀቅ የተያዘውን የአሻጋሪ እቅድ ለማሳካት ወጣቶች ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው መረባረብ አለባቸው ብለዋል።

ዛሬ የተካሄደው መድረክም ይሄን አላማ ለማሳካት መሆኑን አመልክተው በቀጣይም እስከ ቀበሌ ድረስ እቅዱን በማውረድ መግባባት በመፍጠር የተቀናጀና የተናበበ አተገባበር እንዲኖር ይሰራል ነው ያሉት።

በቢሮው የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና የወጣቶች ንቅናቄ ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ አወቀ መንግስቴ ባቀረፉት የውይይት መነሻ ጽሁፍ እንደገለጹት የ25 ዓመቱ አሻጋሪ እቅድ የክልሉን ህዝብ ወደ መካከለኛ ገቢ ለማሸጋገር የሚያስችል ነው።

እቅዱ ከመነሻ ጀምሮ እስከ አተገባበር ድረስ ለወጣቶች ተሳትፎ፣ ተጠቃሚነትና ፈጻሚነት ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑን ጠቁመው በተለይም ወጣት የመንግስት ሰራተኞች ለእቅዱ መሳካት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የአሻጋሪ እቅዱ በሁሉም ዘርፍ ምርታማነትን ማሳደግ፣ ሰላምና ፍትህን ማረጋገጥ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ማበልጸግ፣ ክልልዊ ባህልና እሴትን ማጎልበትና ሌሎች መሰረታዊ አቅጣጫዎችን ያስቀመጠ መሆኑን አስረድተዋል።

ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የመጡት ጽሁፍ አቅራቢ የሻምበል አግማስ (ዶ/ር)፣ ወጣቱ አቅሙን፣ ጉልበቱንና እውቀቱን ለአገር ልማትና እድገት ማዋል እንዳለበት አመልክተዋል።

በመድረኩ ላይ ከክልል ቢሮዎች፣ ወጣት አደረጃጀቶችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም