ቀጥታ፡

በክልሉ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት ባለሀብቶች በተለያዩ መስኮች እንዲሰማሩ ምቹ ምህዳር ፈጥሯል

ወላይታ ሶዶ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት ባለሀብቶች በተለያዩ መስኮች እንዲሰማሩ ምቹ ምህዳር መፍጠሩን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናገሩ።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ፈጣን ዕድገት ለኢንቨስትመንት ተመራጭ መዳረሻ እያደረጋት መምጣቱም ተመላክቷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወላይታ ሶዶ ከተማ በአንድ ባለሀብት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባ ሆቴልን ዛሬ መርቀው ከፍተዋል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህን ወቅት እንዳሉት ለከተሞች እድገትና ለሆቴል ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የግል ባለሀብቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት ባለሀብቶች በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ምህዳር መፈጠሩን ገልጸዋል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ፈጣን ዕድገት ለኢንቨስትመንት ተመራጭ መዳረሻ እያደረጋት መሆኑንም አቶ ጥላሁን ጠቁመዋል።

ዛሬ የተመረቀው "ታከለ ሆቴል"ም በፈጣን የልማት ጉዞ ላይ ለምትገኘው ወላይታ ሶዶ ከተማ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆንና ለሌሎች ባለሀብቶችም መነቃቃት እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የሆቴሉ ባለቤት ከትንሽ ንግድ ሥራ ጀምረው ለትልቅ ደረጃ መድረሳቸው ለሌሎችም ተሞክሮ ይሆናል ሲሉም አቶ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በአገልግሎት፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በሌሎችም የኢኮኖሚ ዘርፎች ለተሰማሩ ባለሀብቶች የቅርብ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ ጠቁመው፣ ሌሎች ባለሀብቶች ያለውን ምቹ ምህዳር ተጠቅመው  ወደክልሉ እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የሆቴሉ መመረቅ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም አበርክቶው የጎላ መሆኑን የተናገሩት የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ እታገኝ ኃይለማርያም  በበኩላቸው በከተማዋ ዕድገት ላይ የግል ባለሀብቶች ሚና የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተማዋ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ኢንቨስትመንት ለመሳብ በተሰራው ሥራ በርካታ ባለሀብቶች የልማት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለሆቴሉ ግንባታ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንና ከ150 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን የተናገሩት ደግሞ የሆቴሉ ባለቤት አቶ ታከለ ቦሼ ናቸው።

በክልሉ ያለው ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር እና በየደረጃው የተደረገላቸው ድጋፍ  ለሥራቸው ውጤታማነት አስተዋጸኦ ማድረጉን የገለጹት ባለሀብቱ፣ ስለተደረገላቸው ሁለንተናዊ ድጋፍም አመስግነዋል።


 

በሆቴሉ ምረቃ መርሃ ግብር ላይ የክልሉ፣ የዞንና የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም