ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት አህጉራዊ የአቪዬሽን ትስስርን የማጎልበት ሚናውን እየተወጣ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፦‎ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት አህጉራዊ የአቪዬሽን ትስስርን የማጎልበት ሚናውን እየተወጣ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ከ12 ሀገራት የተውጣጡ 457 የአቪዬሽን ባለሙያዎችን ዛሬ አስመርቋል።


 

ተመራቂዎቹ 58 ፓይለቶች፣ 115 የአውሮፕላን ጥገና ቴክኒሻኖች እና 284 የበረራ አስተናጋጆች ናቸው፡፡

ከተመራቂዎቹ መካከል ኢትዮጵያ፣ የጣሊያን፣ የካሜሮን፣ ቻድ፣ ጋቦን፣ ማዳጋስካር፣ ማላዊ፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳና የመን ዜጎች ይገኙበታል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ግንባር ቀደም አየር መንገድ እንዲሆን ያስቻሉ በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ከነዚህ መካከል ዋነኛው ከፍተኛ ችሎታ እና ተነሳሽነት ያለው የሰው ሃይል የመመልመል፣ የማሰልጠን እና የማቆየት ችሎታ ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ለበርካታ አስርት ዓመታት ቁልፍ የአቪዬሽን ባለሙያዎችን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በማቅረብ ወሳኝ ሚና መጫወቱን ጠቅሰዋል።

የዛሬዎቹ ተመራቂዎች ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ መሆናቸውን በመጠቆም ይህም አህጉራዊ የአቪዬሽን ትስስርን ለማጎልበት ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለአፍሪካ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ እድገት ያበረከተውን አስተዋፅኦ የሚያሳይ ግልጽ ምስክርነት ነው ሲሉ ዋና ስራ አስፈፃሚው አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለስኬቱ ብቁ የአቪዬሽን ባለሙያዎችን ማፍራት አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ የዩኒቨርሲቲውን አቅም የበለጠ ለማሳደግ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በመመደብ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ላዕከ ታደሰ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአቪዬሽን ስልጠና ለመስጠት በቁርጠኛነት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ አየር መንገድን የሚያገለግሉ ባለሙያዎችን እያስተማርን ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን በአፍሪካ በአቪዬሽን ዘርፍ የሚሰማሩ ባለራዕይ መሪዎችን እያነጽን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ እውነተኛ የፓን አፍሪካ ተቋም የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ተልዕኮ አህጉሪቱ በዘርፉ ያላትን ደረጃ ከፍ አድርጎ ማውጣት ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም